ከንቲባ አዳነች አቤቤ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በበጎ ፈቃደኞች ለአቅመ ደካሞች ነዋሪዎች የታደሱ 69 ቤቶችን አስረከቡ።

 

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሐግብር ለአቅመ ደካሞች ነዋሪዎች የታደሱ 69 ቤቶችን በዛሬው ዕለት አስረክበዋል ።ለቤቶቹ ግንባታ ጉሙሩክ ኮሚሽን የ3 ሚሊየን ብር ድጋፍ ያደረገ ሲሆን ሌሎች ባለሀብቶች እና በጎፈቃደኛ ወጣቶች ተሳትፈዋል ።በርክክብ መርሀግብር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዘንድሮው በከተማችን 2ሺህ ያህል የአቅመ ደካማ ቤቶችን ለማደስ እቅድ ቢያዝም ልዩ ልዩ ተቋማትን ፣ባለሀብቶችን እና በጎፈቃደኞችን በማስተባበር ከ2ሺህ 455 ቤቶችን በአዲስ መልክ አፍርሶ በመገንባት ለነዋሪዎች መሰጠታቸውን ገልጸዋል ።

ህዝባችን በአንድነት መተባበረ እና መተጋገዘ የኢትዮጵያውያን መሠረታዊ መገለጫ ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ በቀጣይም የበጎ ፈቃድ ተግባራትን በማጠናከር ነዋሪዎች አካባቢያቸውን በማልማት፣በማጽዳት እና በማስዋብ ሁሉም ጥረት ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል።

በህውሃት በከፈተው ጦርነት በወሎ እና አካባቢው የተፈናቀሉ ፣በቦረና ደግሞ በድርቅ ሣቢያ የተጎዱ ዜጎችን እንዲሁም የመከላከያ ሰራዊቱን ህዝቡን በማስተባበር የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናግረዋል ።የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ነጻነት ዳባ በበኩላቸው በክፍለ ከተማው በባለፉት የክረምት ወራት 270 የአቅመ ደካማ ቤቶች በአዲስ መልክ ታድሰው ለነዋሪዎች መተላለፋቸውን ገልጸዋል ።

በተጨማሪም የአካባቢን ሰላም በመጠበቅ፣ማዕድ በማጋራት፣ በደም በመለገስ እና በልዩ ልዩ ተግባራት የበጎ ፈቃድ ስራዎች መከናወናቸውን ወ/ሮ ነጻነት ተናግረዋል ።

Share this Post