ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከከተማና መሰረተ ልማት ሚንስትር ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ ጋር በመሆን የተገጣጣሚ ቤት የፈጠራ ቴክኖሎጂ ስራን ጎበኙ።

 

የመገጣጣሚ ቤት ቴክኖሎጂው በከተማዋ በአነስተኛ የኑሮ ደረጃ ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎችን የቤት ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያግዙ መሆናቸውን ከንቲባ አዳነች አቤቤ በጉብኝቱ ወቅት ተናግረዋል ።ቴክኖሎጂው በአነስተኛ ወጪ እና ጊዜ ቤት መገንባት ከማስቻል ባለፈ አካባቢው ለልማት ቢፈለግ በቀላሉ በማንሳት ሌላ ቦታ መስራት ያስችላል ብለዋል።

በኮንስትራክሽን እና ግንባታ ዘርፍ ተመርቀው የተቀመጡ እና ፍላጎት ያላቸውን ወጣቶች በማሰልጠን የስራ ዕድል እንዲፈጠር የከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ከንቲባ አዳነች ገልጸዋል ።መሰል ቴክኖሎጂዎች በከተማዋ በብዛት እንዲስፋፋ እና በቅርቡ ለተጀመረው የአቅመ ደካማ ነዋሪዎች ቤት እድሳት ስራ በጥቅም ላይ እንዲውል ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር በቅንጅት እንሰራለን ብለዋል ከንቲባዋ ።

የከተማና መሰረተ ልማት ሚንስትር ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መሰል የቴክኖሎጂ በማፍለቅ እና ስታንዳርድ በማውጣት የህብረተሰቡን ችግሮች እንዲፈታ ይሰራል ብለዋል፡፡ቴክኖሎጂው በአዲስ አበባ እና በሌሎች ከተሞች መኖሪያ ቤት ችግርን የመቅረፍ እና ለበርካታ ወጣቶች የስራ እድል የሚፈጥር በመሆኑ የክልል ከተሞች ቴክኖሎጂውን እንዲጠቀሙ ይደረጋል ብለዋል።ተገጣጣሚ ቤቶቹ አስተማማኝ እና በአነስተኛ ወጪ በአጭር ጊዜያት መጠናቀቅ የሚችሉ መሆናቸውን የቴክኖሎጂው አፍላቂ ኢ/ር ብርሀኑ ካሳ ገልጸዋል ።የመገጣጠሚያ ቤቱ ያለምንም ኮለን እና ሌሎች የግንባታ ግብዓት ሳያስፈልግ በኮንክሪት እና በቃጫ ብቻ ቤት መስራት የሚያስችል ቴክኖሎጂ ነው።

 

Share this Post