ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ለንግድ ማህበረሰቡ የተሰጠ ማሳሰቢያ

በከተማችን የሚገኙ የንግዱ ማህበረሰብ የተጀመረውን ሁለንተናዊ ለውጥ ቀጣይነት ለማረጋገጥ እና የብልፅግና ራዕያችን እንዲሳካ ከመጀመሪያው ጀምሮ መጠነ ሰፊ ድጋፎችን እያደረገ ይገኛል፡፡

ነገር ግና አንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎች ወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታን ታሳቢ በማድረግ በአቋራጭ ለመክበር እና ሆን ብሎ ህገ -ወጥ የዋጋ ጭምሪ እና ኢኮኖሚያዊ አሻጥር ለመፍጠር ጥረት ማድረግ ላይ መሆናቸው ተደርሶበታል፡፡

ስለሆነም በማንኛውም ንግድ ስራ ላይ ተሰማርታችሁ የምትገኙ ነጋዴዎች ለሽያጭ በሚቀርቡ ማለትም በተለይ ከዉጪ ሃገር የገቡ ወይም በሃገር ውስጥ የተመረቱ ማንኛውም ዕቃዎች የግብርና ምርቶች ፣የምግብ እና መሰል ሸቀጣ ሸቀጦች ማንኛውም አገልግሎቶች እና በመሳሰሉት ላይ ዋጋ መጨመር በጥብቅ የተከለከለ ነው፡፡

በተጨማሪም ምርት መደበቅ እና ማከማቸት፣ ምርትን ከባዕድ ነገር ጋር መቀላቀል፣ ሚዛና ማዛባት፣ ጊዜ ያለፈባቸው ምርቶች ለገበያ ማቅረብ፣ በተመሳሳይ ደረጃ ግብይት መፈጸም፣ ያለደረሰኝ መገበያየት፣ ከአድራሻ ውጪ መገበያየት እና ሌሎች በህግ የተከለከሉ ድርጊቶችን መፈጸም በንግድ ህግ የሚያስቀጣ በመሆኑ ከላይ በተጠቀሱት ህገወጥ ተግባራት የተሳተፋችሁ ነጋዴዎች እና የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ቢሮው በንግድ ምዝገባ እና ፈቃድ አዋጅ 980/2008 መሰረት አሰፈላጊውን እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን በጥብቅ እናሳስባለን፡፡

የከተማችን ነዋሪዎች ይህን ማስጠንቀቂያ ተላልፎ የሚገኙ ህገወጥ ነጋዴዎች በአከባቢው /ለሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ወይም በቢሮው ነጻ ስልክ ቁጥር 8588 ወይም 0111-11-55-81 ደውላችሁ እንድታሳውቁን ትብብራችሁን እንጠይቃለን፡፡ወቅቱ ከትርፋችን በላይ አገራችንና ህዝባችን ስለማትረፍ የምናስብበት ነው!

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ

Share this Post