16
Aug
2021
የመስቀል አደባባይ የመኪና ማቆሚያ አገልግሎት መስጠት ጀመረ:: የመስቀል አደባባይ ፕሮጀክት አካል የሆነው የመኪና ማቆሚያ የ24 ሠዓት አገልግሎት መስጠት መጀመሩን የኤግዚቢሽን ማዕከልና የገበያ ልማት ድርጅት አስታወቀ። ከ2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ተገንብቶ ባለፈው ሰኔ ወር ለምርቃት የበቃው የመስቀል አደባባይ ፕሮጀክት ለ1 ሺህ 400 ያህል ተሽከርካሪዎችን ማስተናገድ አቅም ያለው የመኪና ማቆሚያ የ24 ሠዓት አገልግሎት መስጠት መጀመሩን የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጥላሁን ታደሰ ለኢዜአ ገልጸዋል። በመኪና ማቆሚያው ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል መገልገል እንደሚችል ያስታወቁት ዋና ስራ አስፈጻሚው የንግዱ ማኅበረሰብ ከመኪና ማቆሚያው በተጨማሪ የዲጂታል ማስታወቂያ መጠቀሚያዎችን መገልገል እንደሚችልም ጠቁመዋል። ሐይማኖታዊና ሕዝባዊ በዓላት፣ የሙዚቃ ኮንሰርቶች፣ ሌሎች ማኅበራዊ ሁነቶችና ትርዒቶችን በስፍራው በማዘጋጀት ንግድና ኢንቨስትመንቱን የማሳለጥ ስራው ይጠናከራል ብለዋል። የኤግዚቢሽን ማዕከሉን ለማዘመን፣ ለማልማትና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት መስጠት እንዲችል ለማድረግ በመንግስት ደረጃ ጥናት እየተካሄደ ነው ብለዋል። እንደ አቶ ጥላሁን ገለጻ በማዕከሉ ከሚዘጋጁ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ኤክስፖዎችና ሌሎች የገቢ ማስገኛ አገልግሎቶች በ2014 በጀት ዓመት እስከ 170 ሚሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት ታቅዷል።