የሰነድ ማረጋገጫ ማህተም አሰራርን ከዛሬ ጀምሮ መቀየሩን የአዲስ አበባ ከተማ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ እና መረጃ ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡

 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወሳኝ ኩነት ምዝገባ እና መረጃ ኤጀንሲ እየተበራከተ የመጣውን ሰነድ አስመስሎ የመስራት ወንጀል ለመቀነስ ኤጀንሲው በሚሰጣቸው የልደት፣ የጋብቻ ፣ የፍቺ ፣ የያላገባ እንዲሁም ሌሎች ማስረጃዎች አገልግሎት ሲሰጥበት የነበረውን የማረጋገጫ አሰራር መቀየሩን ገልጿል፡፡

ፎርጀሪ እያደረሰ ያለውን ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጉዳት ለመቀነስ ከዚህ ቀደም የነበረውን የሰነድ ማረጋገጫ አሰራር በዘመናዊ አሰራር በመተካት የበኩሉን ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ነው ኤጀንሲው ያስታወቀው።

ተቋሙ በዋና መስሪያ ቤት የሚሰጠውን ለፖስፖርት አገልግሎት፣ ለውጭ አገራት የቪሳ ጥያቄ ፣ ለተለያዩ የውጭ እና የአገር ውስጥ ጉዳዮች የሚውሉ ማስረጃዎች የሚረጋገጥበትን የቀድሞ የማህተም አሰራር በማስቀረት በውጭ አገር አሰርቶ ባስገባው ዘመናዊ የሆሎግራም ማረጋገጫ አሰራር ከዛሬ ህዳር 13 2014 ጀምሮ በመተካት ተግባራዊ ያደርጋል።

ይህ አሰራር ከፖስፖርት እና ከውጭ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ በየቦታው ተመሳስሎ በመስራት ለማለፍ የሚሞከሩ ሌብነቶች ለመግታት እገዛ የሚያደርግ እንደሚሆንነ ታምኖበታል።

በተያዘው በጀት ተቋሙ የሚሰጣቸውን ሰርተፍኬቶች የደህንነት ደረጃ ከፍ ለማድረግ አዲስ የPersonalization ቴክኖሎጂ ባላቸው ፕሪንተሮች ለመተካት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ኤጀንሲው አመልክቷል ።

Share this Post