የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮችና አካታች ሀገራዊ ምክክር አስፈላጊነት ላይ ተወያይቶ አቅጣጫዎችን አስቀመጠ
የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ዛሬ ኅዳር 30 ቀን 2014 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ የሀገርን ህልውና ለማጽናትና ዴሞክራሲን ለማጎልበት የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን ማስቀመጡን የፓርቲው ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ ገልፀዋል።
እንደ አቶ አደመ ፋራህ ገለፃ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታውን የገመገመ ሲሆን የሀገርን ህልውና ለማስጠበቅ በተደረገው ዘመቻ ''ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት'' የተገኘውን ውጤት አድንቋል።
በዘመቻው አመርቂ ውጤት እንዲገኝ የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣የክልል የጸጥታ ኃይሎች፣ደጀኑ ሕዝብና በአገር ውስጥና በውጭ አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ላደረጉት ርብርብና ከፍተኛ አስተዋጽዖ ኮሚቴው ምስጋና አቅርቧል።
ኅብረተሰቡ ያሳየው ርብርብና ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ይበልጥ እንዲጎለብትና በቀጣይም ሌሎች ድሎች እንዲመዘገቡ በሚያደርግ ሁኔታ ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሥራ አስፈጻሚው ጥሪ ማቅረቡን ኃላፊው ገልፀዋል።እንደ አቶ አደም ፋራህ ገለፃ ከአሸባሪው ወራሪ ነጻ የወጡ አካባቢዎችን መልሶ ለማደራጀትና ለማቋቋም የተጀመረው ሥራ በመልካም ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑን ሥራ አስፈጻሚው የገመገመ ሲሆን ሥራው በተቀናጀ አግባብ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አምኖበታል።ለመልሶ ማቋቋምና ማደራጀት ሕዝቡ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ ሥራ አስፈጻሚው ጥሪ ማቅረቡንም ነው ኃላፊው የገለፁት።
የፓርቲው አመራሮችና አባላትም ለተጀመረው የማደራጀትና መልሶ ማቋቋም እንቅስቃሴ የሚጠበቅባቸውን ሁሉ እንዲያደርጉ አቅጣጫ አስቀምጧል።
በመጨረሻም አቶ አደም ሥራ አስፈጻሚው በሀገራችን የተጀመረውን የፖለቲካ ሽግግር ሂደት ስለሚጠናከርበት ሁኔታም መምከሩን ገልፀዋል።
በዚሁ መሰረተ አካታችነትና ሁሉን አቀፍ ምክክር ከለውጡ መነሻ ጀምሮ ሲቀነቀን የነበረ ሐሳብ መሆኑ የታየ ሲሆን በሀገራችን አካታች ሀገራዊ ምክክር አስፈላጊ መሆኑን አምኖበታል ብለዋል።አካታች ሀገራዊ ምክክሩም ሀገር በቀል የሆነ፣በመሰረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር የሚያግዝ፣ ከሕዝባችን ባህልና ዕሴት ጋር የሚጣጣም፣ የሀገራችንን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት በዘላቂነት ለማስከበር የሚረዳ መሆን እንዳለበት አጽንዖት ተሰጥቶታል ብለዋል።
የታሰበው ሀገራዊ ምክክር እንዲሳካም በገለልተኛ የሆነ ብቃት ያለው ሀገራዊ ተቋም መመራት እንዳለበት ሥራ አስፈጻሚው አምኖበታል ብለዋል።አካታች ምክክሩ እንዲሳካና የሚፈለገውን ውጤት እንዲያመጣም ብልጽግና ፓርቲ እንደመሪ ፓርቲ የሚጠበቀበትን ኃላፊነት እንደሚወጣ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ማረጋገጡንም ኃላፊው አክለው ገልፀዋል።