የብሬክስሩ ኒውስ ጋዜጠኞች የአዲስ አበባን ሰላማዊነት ለዓለም እያሳዩ ናቸው

 

********************************

የምዕራባውያኑ መገናኛ ብዙሃን ከዓለም የሚደብቁትን እውነታ በመግለጥ የሚታወቁት የብሬክስሩ ኒውስ ጋዜጠኞች ወደ አዲስ አበባ በመምጣት የከተማዋን ሰላማዊነት ለዓለም እያሳዩ ናቸው።

ጋዜጠኛ ኢዩጂን ፒሩየር እና ራኒያ ካሌክ አዲስ አበባ መግባታቸውንና በሚቀጥሉት ቀናት ስለ አፍሪካ ቀንድ እውነተኛ ዘገባዎችን ለዓለም እንደሚያደርሱ ተናግረዋል።አንድነት ፓርክንና የወዳጅነት አደባባይን ጨምሮ ከተማዋን ተዘዋውሮ የተመለከተው ጋዜጠኛ ኢዩጂን “ስለ አዲሰ አበባ ሊዘገብ የሚችለው ሰላማዊ እና በፈጣን እንቅስቃሴ ውስጥ መሆኗን ብቻ ነው” ብሏል።አያይዞም የወዳጅነት አደባባይ ሰርገኞችን እና ሌሎች ጎብኚዎችን እያስተናገደ ስራ ብዙ መሆኑን በምስል አስደግፎ አቅርቧል።

ራኒያ ካሌክ በበኩሏ “አዲስ አበባን ተዘዋውረን አይተናታል የውጭ መገናኛ ብዙሃኑ እንደሚያናፍሱት በህወሃት እጅ ለመውደቅ የተዘጋጀች አሊያም የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት እንደሚያስጠነቅቀው የተረበሸች ወይም የምታስፈራ ከተማ አይደለችም ብላለች” የመዲናይቱን ሰላማዊነት ስትገልፅ።

ቢቲ ኒውስ በወቅታዊ የኢትዮጵያ ሁኔታ ላይ እውነትን ለዓለም የገለጡ በርካታ ጥንቅሮችን በማዘጋጀት ማሰራጨታቸውን ከብሬክስሩ ኒውስ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።የምእራቡን ዓለም ሴራ የሚያጋልጡ ዘገባዎችን በመስራት ነፃ ድምፅ መሆኑ የሚነገርለት ይህ ሚዲያ ቀጥታ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት የሀገሪቱን ትክክለኛ ገፅታ ለዓለም ለማሳየት የራሱ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ይጠበቃል።

Share this Post