በጉባኤው ላይ ተገኝተው መልእክት ያስተላለፉት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የአዲስ አበባ ሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ቦርድ ሰብሳቢ ብጹህ አቡነ መልከጸዲቅ የሃይማኖት ተቋማት ስለ ኢትዮጵያ ሠላም በመስበክ መልዕክቶችን በአደባባይ ጭምር ሲያስተላልፉ መቆየታቸውን ጠቅሰው በተለይ በሠላም እሴት ግንባታ፣ በስነ-ምግባርና የሞራል ግንባታ ላይ በማተኮር ውይይቶችና ስልጠናዎች መካሄዳቸውን ተናግረዋል።ሀገርን ማልማት እና ማሳደግ ለመንግስት ብቻ የሚተው አይደለም ያሉት ሰብሳቢው ቤተ-እምነቶች በሰብዓዊ ድጋፍን ጨምሮ በአረንጓዴ አሻራ እና በሌሎች የልማት ስራዎች ላይ እየተሳተፉ መሆኑን ገልጸዋል ።
የሃይማኖት ተቋማት በቀጣይም ሀገራዊ አንድነትን በሚያጠናክሩና ትውልድን በስነ-ምግባር በሚያንፁ ስራዎች ላይ አተኩረው እንደሚሰሩ ብጹህ አቡነ መልከጸዲቅ ጠቁመዋል ።የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ምክትል ቢሮ ሃለፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ በበኩላቸው የሀይማኖት አባቶች ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ፣የመቻቻልና መከባበር እሴቶችን በማስተማር የጋራ እሴቶቻችን እንዲጎለብቱ የጀመሩትን ስራ አጠናክሮ ሊቀጥሉ እንደሚገባ ገልጸዋል ።
በተጨማሪም የአሸባሪው የህወሓት ቡድን እያደረሰ ያለውን ጦርነት ሸሽተው ለተፈናቀሉ ወገኖች እና የሀገርን ህልውና ለማስጠበቅ መስዕዋት በመክፈል ላይ የሚገኘውን የሀገር መከላከያ ሰራዊት ጉባዔው የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ምክትል ሃላፊዋ ጥሪ አቅርበዋል ።
የአዲስ አበባ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ፀኃፊ መጋቢ ታምራት አበጋዝ ሰባቱ የእምነት ተቋማት ላለፉት አስርት ዓመታት ጥምረት ፈጥረው ትውልዱን ከማነፅ ባለፈ ከከተማ አስተዳደሩ ጎን በመሆን በልዩ ልዩ ተግባራት ተሳትፎ አድርገዋል ፤ይህንንም አጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
እንደ ሀገር ያጋጠመውን ወቅታዊ ችግርን በመገንዘብ በየቤተእምነቶች በተናጠል ከሚከናወነው ጸሎት ባለፈም የጋራ ጸሎት መካሄዱን የተናገሩት ደግሞ የአዲስ አበባ እስልምና ከፍተኛ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዘዳንትና ጉባኤ ምክትል የቦርድ ሰብሳቢ ሼህ አሊ መሀመድ የተረጋጋ ሰላም በከተማዋ እንዲፈጠር ህብረተሰቡን የማስተማርና የማስገንዘብ ስራዎችን ተሰርቷል ብለዋል ።