16
Sep
2021
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአማራ ክልል አሸባሪው የህወሓት ቡድን በፈጸመው ወረራ ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች ለማገዝ የ350 ሚሊየን የጥሬ ብር እና የ35 ሚሊየን 134 ሺህ 128 የአይነት በጠቅላላው 385 ሚሊየን 134 ሺህ ብር ድጋፍ አድርጓል፡፡ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በባህርዳር ከተማ በመገኘት ለአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አገኘሁ ተሻገር አስረክበዋል ።አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በአማራ እና አፋር ክልሎች ላይ በከፈተው ወረራ ንጽሐን ተገድለዋል፣ የአካል ጉዳት አድርሷል ያሉት ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ የአዲስ አበባ ሕዝብ እና የከተማ አስተዳደሩ ከጎናችሁ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ድጋፉን አበርክተናል ብለዋል።
ድጋፉ ከከተማዋ የመንግስት ሰራተኞች፣የንግዱ ማህበረሰብ እና ከልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሰበሰበ መሆኑን ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል ።የከተማ አስተዳደሩ በቀጣይም በጦርነቱ ሳቢያ ከቀያቸው የተፈናቀሉ እና የተጎዱ ዜጎችን በዘላቂነት ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ጠቁመዋል ።የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር በበኩላቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጦርነቱ የተጎዱ ዜጎችን ለማገዝ ላደረገው ድጋፍ አመስግነዋል ።