የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከህብረተሰቡ ያሰባሰበውን ሰንጋ በሬዎችን ጨምሮ ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የአይነት ድጋፍ ለአማራ ክልል አስረከበ፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳ...

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከህብረተሰቡ ያሰባሰበውን ሰንጋ በሬዎችን ጨምሮ ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የአይነት ድጋፍ ለአማራ ክልል አስረከበ፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አሸባሪው የህውኃት ቡድን በኢትዮጵያ አንድነት ላይ የቃጣውን የሽብር ተግባር ለመመከት ከሰሞኑ ከህብረተሰቡ ያሰባሰበውን ሰንጋ በሬዎችን ጨምሮ የተለያዩ የምግብ ቁሳቁሶችን ለሀገር መከላከያ ሚኒስቴር ማስረከቡ ይታወሳል፡፡ በዛሬው ዕለትም የከተማ አስተዳደሩ ለአማራ ክልል በጎንደር በኩል ባለው የሕልውና ዘመቻ በግንባር በመገኘት ከባለሃብቶች እና ከነዋሪዎች የተሰበሰበውን 139 ሰንጋ፣ 1 ሺህ 809 በግና ፍየል፣ ጤፍ፣ በሶ፣ ማካሮኒ፣ በቆሎ፣ ሩዝ እና ሌሎች ምግብነክ ቁሳቁሶችን አስረክቧል፡፡ ከከተማ አስተዳደሩ የተደረጉትን ድጋፎች የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘላለም ሙላቱ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ ዶ/ር ሙሉነሽ አበበ አስረክበዋል፡፡ አሸባሪው የህውሃት ቡድን በአማራ ክልል ላይ በሰነዘረው ጥቃት ለተጎጂዎች ድጋፍ በማድረግ እና በክልሉ የነበሩ ተፈናቃዮችን ለመደገፍ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ድጋፍ ማድረጉን አቶ ዘላለም ሙላቱ ለአብነት አንስተዋል፡፡ አዲስ አበባ የኢትዮጵያውያን መዲናነቷን በተግባር ስታረጋግጥ ይህ ድጋፍ የመጀመሪያዋ አይደለም ያሉት አቶ ዘላለም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና ነዋሪዎቿ ዘመቻው በድል እስኪጠናቀቅ ድረስ አጋርነታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል፡፡ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ ዶ/ር ሙሉነሽ አበበ በበኩላቸው አሸባሪው የህውሃት ቡድን የሁሉም ኢትዮጵያዊ የሕልውና ስጋት መሆኑንም ጠቅሰው ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች በየአቅጣጫው የሚያደርጉት ድጋፍ እና ተነሳሽነት ለኢትዮጵያ ትንሳኤ ተስፋ ሰጭ ነው ብለዋል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ላደረገው ድጋፍ እና ላሳየው አጋርነት የአማራ ክልል መንግሥት ምስጋና እና እውቅና ይሰጣል ብለዋል፡፡

Share this Post