የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ፣የሴክተር ተቋማት አመራሮች እና የክፍለከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚዎች በተገኙበት የ2013 በጀት ዓመት የሰራ አፈጻጸም ግምገማ በመካሄድ ላይ ነው ። ግምገ...

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ፣የሴክተር ተቋማት አመራሮች እና የክፍለከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚዎች በተገኙበት የ2013 በጀት ዓመት የሰራ አፈጻጸም ግምገማ በመካሄድ ላይ ነው ። ግምገማውን ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ፣ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪዉ አቶ ጃንጥራር አባይ እንዲሁም በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የማዘጋጃ ቤታዊ ስራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነ በተገኙበት እየተካሄደ ይገኛል። በዚህም በበጀት ዓመቱ የተከናወኑ አበይት ዋና ዋና ተግባራት አፈጻጸምና በሂደቱም የታዩ ጠንካራ አፈፃፀሞችና ክፍተቶች ቀርበው ሰፊ ዉይይት እየተካሄደባቸው ይገኛል። በዋናነትም የከተማዉን ህብረተሰብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ግዙፍ ፕሮጀክቶች የተከናወኑ ሲሆን ህገወጥ የመሬት ወረራ ፣በጋራ መኖሪያ ቤቶች እና በቀበሌ ቤቶች በኩል የሚስተዋሉ ብልሹ አሰራሮችን ከመግታት አንጻር አበረታች ዉጤት መመዝገቡ በግምገማዉ ላይ ቀርቧል። በበጀት ዓመቱ በተለይም በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ዉህደትና ቅንጅታዊ ስራዎች ፤ ህብረተሰቡን በማስተባበር ለሀገር መከላከያ ሰራዊት እና ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የተደረገዉ ድጋፍ፤ የአካባቢ ጽዳት ፣የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ፣የአረንጓዴ ልማት እና ሌሎች መርሐግብሮች ላይ የተከናወኑ ተግባራት ለቀጣይ ሰራዎች በጥንካሬ መንደርደሪያ እንደሚሆን ተጠቁሟል ። ተቋማዊ አሰራርን ለማጠናከር እና በህብረተሰቡ በኩል የሚነሱ የአገልግሎት አሰጣጥ እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለማፍታትም በየደረጃው የሚገኝ አመራር በልዩ ትኩረት መስራት እንዳለበት በግምገማው ተመላክቷል። ዉይይቱ ከሰዓትም የሚቀጥል ሲሆን በቀጣይ አስር ዓመታት የከተማዋን ሁለንተናዊ እድገት እና የነዋሪዎቿን አዳጊ ፍላጎት ባማከለ መልኩ በሚተገበሩና ከተማዋ የጀመረችውን የብልጽግና ጉዞን ማረጋገጥ በሚያስችሉ አብይት ተግባራት ዙሪያ በሚካሄዱ ሰፊ ዉይይቶች የሚቀጥል ይሆናል ።

Share this Post