የአዲስ አበባ ዩኒቨረሲቲ እና የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ በቤት ልማት ዘርፍ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ፡፡

 

የአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ እና የአዲስ አበባ ሣይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ዘርፍ በጋራ ለመሥራት መዘጋጀታቸውን አስታወቁ፡፡በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወ/ሪት ያስሚን ወሀብረቢ የመግባቢያ ስምምነቱ በተፈረመበት ወቅት ባደረጉት ንግግር ቢሮውና ተጠሪ ተቋሙ የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያለውን የህብረተሰብ ክፍል የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ ከዩኒቨርስቲው ጋር በቅርበት መሥራት የጎላ አስተዋፅኦ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡

የአዲስ አበባ ሣይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ዘርፍ ደረጃውን የጠበቀ የዲዛይን ሥራዎችን ጥናት በማድረግ፥ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማስረፅ የተሻለ ስኬት ማስመዝገብ ይቻላል ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ሣይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር አብርሃም ደበበ ዩኒቨርስቲው የህብረተሰቡን የዕለት ተዕለት ህይወት ከሚመለከት አበይት የልማት ሥራዎች መካከል የቤት ልማት ፕሮግራሙ አንዱ በመሆኑ ዩኒቨርስቲው ከቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ጋር በቅርበት ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል።ዩኒቨርስቲው በዝቅተኛ ወጪ ለህብረተሰቡ ተደራሽ ቤቶችን ለመገንባት የሚያስችሉ ጥናቶችን በማካሄድና የማማከር አገልግሎት በመስጠት እንዲሁም ነፃ ለሙያተኞቹ የትምህርት ዕድል በማመቻቸት ከቢሮው ጋር በቅርበት ይሠራል ብለዋል።

ዶ/ር አብርሃም በሁለተኛ እና ሦስተኛ ዲግሪ መርሃ ግብር የሚያሰለጥናቸው ተማሪዎችም የጋራ መኖሪያ ቤቶች እየተገነቡባቸው በሚገኙት ሳይቶች በመገኘት የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን አስመልክቶ ተግባራዊ ስልጠና ለመከታተል ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርላቸው ገልፀዋል፡፡

Share this Post