ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በአዲስ አበባ ምክር ቤት የከተማው ከንቲባ ሆነው ቃለ መኃላ በፈጸሙበት ወቅት ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት የከተማዋን ትልቅነት የሚመጥን ስራ እንደሚሰሩ ጠቅሰው ኢትዮጵያ የምንወዳት እንደ ዓይናችን ብሌን የምንሳሳላት አገራችን ብትሆንም በውስጥና በውጭ ሃይሎች ጫና ምክንያት ያላትን ሀብት ሳትጠቀም በድህነት ስትዳክር ኖራለች ብለዋል፡፡
የከተማዋን ብልጽግና ለማሳካት የህብረተሰቡን ኣዳጊ ፍላጎት ታሳቢ በማድረግ በትጋት እንሰራለን ያሉት ከንቲባዋ በከፍተኛ ድህነት ውስጥ የሚኖረውን የኑሮ ውደነት ዋና ገፈት ቀማሽ የሆነውን በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚኖረውን ህዝብ ከድህነት ለማውጣት በቁርጠኝነት እንሰራለን ብለዋል፡፡
ከንቲባዋ እንዳሉት ሀብት በመፍጠርና ውጤታማ የሆነ አጠቃቀምን በመጠቀም ሁሉም ዜጎች ተጠቃሚ የሚሆኑበትን መንገድ እንከተላለን ያሉ ሲሆን በዚህም የብልጽግና ጉዟችን ሰው ተኮር ነው፤ የከተማዋን የማደግ አቅም ለይተን ቀልጣፋ አገልገሎት እንዲኖር እንሰራለንም ብለዋል፡፡
ከንቲባዋ አክለውም የመሰረተ ልማት፣ የመኖሪያ ቤት አቅርቦት፣ የውሃና መብራት ስልክ አገልገሎትን ለማሳደግ በትጋት እንሰራለን ሲሉ ተናረዋል፡፡
ከንቲባዋ እንዳሉት ለወጣቶችና ለሴቶች ልዩ ትኩረት ሰጥተን ርብርብ እናደርጋለን፤ የስራ ፈጠራና ኢንዱስትሪ ልማት ላይ ትኩረት ሰጥተን እንሰራለን፤ የህግ የበላይነትን ለማስከበር በቁርጠኝነት እንሰራለን፤ ህዝቡ የሚሳተፍባቸው የተለያዩ አደረጃጀቶችን እንተገብራለን፤ ጥራትና ተደራሽ የሆነ የጤና ስርአት እንተገብራለን፤ ጥራቱ የተጠቀበቀ ትምህርትን እንተገብራለን፤ አረጋዊያንን ታሳቢ ያደረገ ማህበራዊ አገልገሎት ተደራሽ እናደሀጋለን፤ አዲስ አባባን የባህል ማዕከል እናደርጋታለን ሲሉም ተናግረዋል፡፡ከንቲባዋ አዲስ አበባችንን በአዲስ አስተሳሰብ አፍሪካዊት የብልጽግና ተምሳሌት እንድናደርጋት የላቀ ርብርብ እንድናደርግ ጥሪዬን አቀርባለሁም ብለዋል፡፡
ከንቲባዋ በመጨረሻም ለአዲስ ምዕራፍ መነሻ የሆናችሁ የከተማዋ ነዋሪዎች በ ሙሉ ላደረጋችሁልን ድጋፍ፤ እምነታችሁን ስለሰጣችሁን እናመሰግናለን፤ ዋናው አለቃችን የከተማዋ ነዋሪዎች ናችሁና ድገፋችሁ እንዳይለየን ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
"አዲሱ የከተማ አስተዳደር ከተማዋ ለሁላችንም ትበቃለች የሚል ጽኑ እምነት ይዞ የእጦት እና ስግብግብነትን አስተሳሰብ በመሻገር ለሁሉም ዜጎች የምትሆንና ነዋሪዎቿ ሁሉ ተደስተውባትና ምቾታቸው ተጠብቆ የሚኖሩባት ከተማ ለማድረግ በብርቱ እንሰራለን ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡