የግል ትምህርት ተቋማት የአገልግሎት ክፍያ ጭማሪን በተመለከተ ከአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ የተሰጠ መግለጫ፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውስጥ የሚገኙ የግል ትምህርት ተቋማት በትምህርቱ መስክ በመሰማራት የትምህርት ተደራሽነትን ከማረጋገጥ እና ለከተማዉ ነዋሪ የስራ እድል ከመፍጠር እረገድ ሚናቸዉ ላቅ ያለ ነዉ፡፡ እንዲሁም የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በተከሰተበት ወቅት የተቀመጠዉን ፕሮቶኮል በማክበር የመማር ማስተማሩ ሂደት እንዲከናወን እና ተማሪዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ላደረጉት ስራ እውቅና እንሰጣለን ፡፡በተጨማሪም ማዕድ በማጋራት የአቅመ ደካሞችን ቤት በማደስ መልካም ስራ ውስጥ በመሳተፍ የበርካቶችን እንባ አብሰዋል፡፡ በሌላ መልኩ ለመከላከያ ሰራዊትም የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ መንግስት ለጀመረዉ ህግ የማስከበር ተግባር አጋርነታቸዉን አሳይተዋል፡፡ ይህም የኛ የኢትዮጵያዉያን የመረዳዳት እሴታችን ማሳያ ነዉ፡፡

ይሁን እንጂ 2014 . የትምህርት ዘመን ለትምህርት አገልግሎት እና መዝገባ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት እና ስልጠና ጥራት የሙያ ብቃት ምዘና እና ማረጋገጫ ባለስልጣን ባወጣዉ የማስፈጸሚያ ማኑዋል መስረት መስራት እየተገባቸዉ ባለመፈጸም በርካታ በመቶዎች የሚቆጠሩ ትምህርት ቤቶች የተጋነነ ዋጋ ጭማሪ አድርገዋል፡፡ለቢሮዉ እና ለወላጅ ምላሽ በመስጠታቸዉ እና የማስተካከያ እርምጃ በመውሰዳቸዉ 41 ትምህርት ተቋማት ላይ ተጥሎ የነበረዉ እገዳ እንዲነሳላቸዉ እና አገልግሎት እንዲሰጡ ተደርጓል፡፡

ኢትዮጵያዊ የጨዋነትና አብሮነት እሴቶችን በማዳበር ይህን ወሳኝና አስቸጋሪ ጊዜ በጋራ ማለፍን ማዕከል በማድረግ ሁሉም የትምህርት ባለድርሻ አካላት የበኩሉን ሚና እንዲወጣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ጥሪዉን ያቀርባል አሁን ባለንበት ወቅት ተደጋግፈን የምናልፍበት እንጂ አንዱ በሌላዉ ላይ ጫና የሚፈጥርበት እንዳልሆነ ታውቆ የግል ትምህርት ቤቶች ከደንበኞቻቸዉ ጋር በመነጋገር እና በመግባባት እንዲሰሩ እያሳስብን በቀጣይም ይህን አልፈዉ በሚቀርበዉ ጥቆማ መሰረት ተገቢ ያልሆነ ጫና እና የክፍያ ጭማሪ የሚፈጽሙ የግል ትምህርት ቤቶች የሚኖሩ ከሆነ ፈጣንና የማያዳግም እርምጃ ቢሮው የሚወስድ መሆኑን እንገልጻለን ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ

Share this Post