‹‹ኢትዮጵያ በታሪኳ ገጥሟት የማያውቅ ፈተና ውስጥ ሆና በድል አድራጊነት ፈተናውን እየተወጣች ትገኛለች›› ከንቲባ አዳነች አቤቤ

 

ከንተባ አዳነች አቤቤ በከተማዋ ከፑሽኪን አደባባይ ጎተራ ፤ ከቦሌ ሚካኤል ቡልቡላ ፤ ከቦሌ አየር ማረፊያ ጎሮ እየተከናወኑ የሚገኙ የተለያዩ የመንገድ ፕሮጀክቶችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡በጉብኝቱ ወቅትም ኢትዮጵያ በታሪኳ ገጥሟት የማያውቅ ፈተና ውስጥ ሆና በድል አድራጊነት መንፈስ ፈተናውን እየተወጣች ትገኛለች ያሉት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ከበርካታ ፈተናዎች አንዱ በድል እየተጠናቀቀ የሚገኘው የግምባሩ ፈተና ሲሆን ፤ በግምባር እየተቀዳጀን ያለነውን ድል በከተማው ውስጥ በጀመርናቸው ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ላይም እየደገምናቸዉ እነገኛለን ብለዋል ፡፡

ወራሪው ቡድን ከተማችን አዲስ አበባን ከብቤያለሁ ብሎ ማስወራት ብቻ ሳይሆን በተለያየ መንገድ ችግር ውስጥ እንድንገባ አድርጎ ሲሰራና የሀሰት የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ሲያካሄድ እንደነበር የገለጹት ከንቲባዋ ከየትኛውም ጊዜ በተለየ የተነሳሽነት ስሜት በከተማዋ የሚገኙ አብዛኛው ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ እየተከናወኑ ሲሆን፤ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶችን በተመለከተ በተለየ እልህና ወኔ የድል አድራጊነት መንፈስ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል ፡፡

ይሄንን የምናደርግበት ዋነኛው ምክኒያት ደግሞ እንደ ሀገር ያለንበትን ሁኔታ ከመገንዘብ የመነጨ ሲሆን፤ ለፕሮጀክቶች ስኬት እዚህ ደረጃ መድረስ የግንባሩ ድል ትልቅ አቅም ሆኖናልም ነዉ ያሉት ፡፡ጠላቶቻችን በተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች እንድንንኮታኮት ይፈልጋሉ ያሉት ከንቲባ አዳነች ለዚህም በታሪካዊቷ ከተማ ላሊበላ በሚገኘው አየር ማረፊያ ላይ እና ወራሪው ቡድን ይዟቸው በነበሩ አካባቢዎች በሚገኙ የመሰረተ ልማት አውታሮች ላይ ያደረሰው ውድመት ትልቅ ማሳያ ነው ብለዋል ፡፡

ይሁን እንጂ በከተማችን የሚገኙ ፕሮጀክቶች በላቀ ሁኔታ በመጠናቀቅ ላይ ይገኛሉ በማለት የተናገሩት ከንቲበ አዳነች በተለይም መንገዶች በሚገነቡበት አካባቢ ያሉ ነዋሪዎች በከፍተኛ ተነሳሽነትና የሐገር ፍቅር ስሜት በወሰን ማስከበር ሂደት ውስጥ ያሳዩት ተባባሪነት እጅግ የሚያሥመሰግን ተግበር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም የመንገዶች ባለስልጣን ሰራተኞች ፤ አመራሮች እንዲሁም ተቋራጮች ፕሮጀክቶችን በፍጥነት ከማጠናቀቅ ባሻገር ለጀግናው የሐገር መከላከያ ሰራዊትና ለጸጥታ ሀይሉ ከፍጠኛ መጠን ያለው ሀብት በማሰባሰብና ድጋፍ በማድረግ ደጀንነታቸውን ያስመሰከሩ ሲሆን ግንባር ድረስ በመዝመት ባሳዩት ቁርጠኝነትም ትልቅ ድጋፍ አድርገዋል ብለዋል ከንቲባ አዳነች፡፡የአዲስ አበባ የመንገዶች ባለስልጣን ሀላፊ ኢንጅነር ሞገስ ጥበቡ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ፕሮጀክቶቹ የከተማውን የመንገድ ሽፋን ከማሳደግ በተጨማሪ የከተማዋን የትራፊክ ፍሰት በማሻሻል ትልቅ አስተዋጽኦ የሚኖረው ሲሆን፤ የመንገደቹ ግንባታ ወጪ ሙሉ በሙሉ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሽፋን የተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

Share this Post