የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለአፋር ክልል የ200 ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረገ።

ምክትል ከንቲባ / አዳነች አቤቤ በሰመራ ከተማ በመገኘት ለአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሀጂ አወል አርባ ድጋፉን አስረክበዋል

የአፋር ህዝብ የጁንታው እቅድ እንዳይሳካ እና ኢትዮጵያን

ለመበታተን የሸረበው ሴራ በማክሸፍ በኩል ያበረከተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ምክትል ከንቲባ / አዳነች አቤቤ ገልጸዋል

ምክትል ከንቲባ / አዳነች አቤቤ እንዳሉት አሸባሪው የህወሃት ቡድን የከፈተው ጦርነት አንድ ወይም ሁለት ክልል ላይ ብቻ ሳይሆን መላው ኢትዮጵያዊያን ላይ በመሆኑ በጋራ መረባረብ ይገባናል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያዊነት እንዳያብብ እና አንድነታችን ተጠብቆ ከትውልድ ወደትውልድ እንዳይሸጋገር በማድረግ እኩይ የሆነ ተግባራቸውን ማፈራረስ እና ተግባራዊ እንዳያደርጉት በማድረግ በኩል አብረን የቆምን ቢሆንም ድንበር ላይ ያላችሁት ግን በዋናነት እናንተ የአፋር ክልል ህዝቦች ችግሩን ተጋፍጣችኋል፤ እኩይ ተግባሩ እንዳይሳካም ከመከላከያ ሰራዊታችንና ከፀጥታ ሀይላችን ጋር በመሆን ታሪክ የማይረሳው ተጋድሎ ማድረግ ችላችኋል ብለዋል፡፡

ምክትል ከንቲባዋ አክለውም አሸባሪው ቡድን በአፋር በኩል በተለይም የጅቡቲን መስመር የመዝጋት እቅዳቸውን እንዳያሳኩ ያደረጋችሁትን የጀግንነት ተግባር የጠላትን ቅስም የሰበረ፤ ወገንን ደግሞ ያኮራ ነው፡፡ አሸባሪው ቡድን በየትኛውም ግንባር ማይሳካለት መሆኑን ያሳዬ ተግባር ነበርም ብለዋል፡፡

በዚህ ሂደት ውስጥ ብዙ የዜጎች መፈናቀል ደርሷል፤ ብዙ ጉዳት ደርሷል፤ የወገናችን ጉዳት ያመናል፤ ይሰማናል፤ በአፋር የደረሰው መፈናቀል እያንዳንዳችን እንደተፈናቀልን ይቆጠራል፤ እናንተ በከፈላችሁት መስዋዕነት እኛ በሰላም ወጥተን ስለገባን የተለዬ ምቾት አይሰማንም፤ ስለሆነም በምትፈልጉን ሁሉ ከጎናችሁ እንደሆንን ልንገልጽላችሁ እንወዳለን ብለዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩም በጦርነቱ የተፈናቀሉ ዜጎችን ለማገዝ ከነዋሪዎች ያሰባሰበውን 150 ሚሊዮን በጥሬ ብር እና 50 ሚሊዮን ብር የሚገመት የአይነት በጠቅላላው 200 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን / አዳነች አቤቤ ተናግረዋል

Share this Post