እኛ ለአብሮነታችን እና ለፍቅራችን እንጂ ለጥላቻ ጊዜ የለንም፡- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

 

ሕብረተሰብ አቀፍ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ (ማስ ስፖርት) ከንቲባ አዳነችን አቤቤ ጨምሮ ሌሎችም የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተሳተፉበት በመስቀል አደባባይ ተደረገ።

አዲስ አበባ የሰላምና የአብሮነት ከተማ በሚል መሪ ሃሳብ ሕብረተሰብ አቀፍ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በስፋት በተሳተፉበት በዛሬው ማለዳ በመስቀል አደባባይ ተካሂዷል።

ከንቲባ አዳነች በአካል ብቃት እንቅስቃሴው ላይ እንዳሉት አዲስ አበባ የሰላም ፣የፍቅር ፣የአብሮነትና የኢትያዊነት መገለጫ ከተማ ናት ብለዋል።

ሁላችንም በጋራ በያለንበት አካባቢ የሕብረተሰብ አቀፍ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ልማድ በማድረግ አንድነታችንን ልናጠናክር ይገባል ብለዋል ከንቲባ አዳነች።

እኛ ለአብሮነታችን፥ ለፍቅራችን እንጂ ለጥላቻ ጊዜ የለንም ያሉት ከንቲባ አዳነች የግጭት ነጋዴዎች በፍፁም አዲስ አበባ ላይ ሊፈነጩ አይችሉም ብለዋል፡፡

አዲስ አበባ ለየትኛውም የኢትዮጵያ አካባቢ ምሳሌ ናት፥ ህዝቦቿ በፍቅር፥ አብሮነት ያለምንም ልዩነት አብሮ በመኖር ምሳሌ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡

የከተማችን ነዋሪዎች ሕብረተሰብ አቀፍ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን አዘውትረን ከመስራታችን ጎን ለጎን የመለያየትና የግጭት ጠማቂዎችን እምቢ ልንላቸው ይገባል ብለዋል።

Share this Post