ኢትዮጵያ በኃይል እና በወረራ ማሳካት የምትፈልገው ጉዳይ የለም - ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ

ኢትዮጵያ ማንንም ሀገር ወራ አታውቅም አሁንም የመውረር ፍላጎት የላትም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ116ኛው የመከላከያ ሠራዊት ቀን ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት መከላከያ ሰራዊት በሄደበት ሁሉ አርሶ አደር የሚያግዝ፣ ትምህርት ቤት እና ጤና ጣቢያ የሚገነባ የሰላም እና የልማት ምልክት ነው ብለዋል፡፡

ሰራዊቱ ከኢትዮጵያዊነት ያነሰ ዓላማ የለውም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር እና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መከላከያ ሰራዊት ታሪክ ጠገብ ተቋም መሆኑንም አንስተዋል፡፡

መከላከያ የሰላም ኃይል ሲሆን ዋና ዓላማውም ሰላምን ማጽናት እንደሆነ ገልጸዋል፡

መከላከያ ሰራዊት ያለን ሰላም እንዳይጠፋ ለማስጠበቅ፣ የጠፋ ሰላምን ለመመለስ እና የመጣ ሰላምን ለማጽናት ህይወቱን ይገብራል፤ ደሙን ያፈሳል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት በመከላከያ ሰራዊቱ ውስጥ የተለያዩ ሪፎርሞች የተደረጉ ሲሆን በተለይ ሀገራዊ አስተሳሰብ እንዲይዝ፣ በተለያዩ ጠንካራ አደረጃጀቶች እንዲዋቀር እና በማድረግ አቅም ዙሪያ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን እንዲታጠቅ ሰፊ ስራ ተሰርቷል ነው ያሉት፡፡

Share this Post