"ብልፅግና ፓርቲ ጠንካራ የፓርቲ ቁመና በመፍጠርና ጠንካራ መንግስት በመገንባት የሀገራችንን ብልፅግና እውን ለማድረግ በትኩረት እየሰራ ነው:-

አቶ አደም ፋራህ የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት

የብልፅግና ፓርቲ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የአዲስ አበባ ከተማ የብልፅግና አመራሮች ስብሰባ በፓርቲው ዋና /ቤት በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

ስብሰባውን እየመሩ ያሉት የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንትና የዋና /ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ ብልጽግና ፓርቲ ባስመዘገባቸው ስኬቶች፣ ባጋጠሙ ፈተናዎችና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ በመምከር በየደረጃው የሚገኘውን አመራር የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት ይበልጥ ለማጠናከር እንዲቻል ውይይቱን ማካሄድ እንዳስፈለገ ተናግረዋል፡፡

በሀገራችን እየተስተዋሉ ካሉ ፈተናዎች ውስጥ አንዱ በተለያዩ የፖለቲካ ተዋንያን በኩል የሚታየው በነጻነት አጠቃቀምና በነጻነት አስተዳደር መካከል ሚዛን ያለመጠበቅ መሆኑን ያነሱት ምክትል ፕሬዝዳንቱ ይህን በማረም ረገድ የፖለቲካ አመራሩ ድርሻ ጉልህ እንደሆነ አንስተዋል፡፡

በሀገራችን የግለሰብ እና የቡድን መብቶች የተፈቀዱና ህገ መንግስታዊ ጥበቃ ያላቸው ቢሆኑም በአተገባበር በኩል ችግሮች እንደሚስተዋሉም ገልጸዋል፡፡ በነጻነት ልምምድ ስም የህግ የበላይነትን የሚሸረሽሩና የዜጎችን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ እንቅስቃሴዎች እንዳይፈጠሩ መከላከል የአመራሩ ሃላፊነት መሆኑንም አሳስበዋል፡፡

ብልፅግና ፓርቲ በዚህ መነሻነት በጠንካራ የፓርቲ ቁመናና በጠንካራ መንግስት ግንባታ የኢትዮጵያን ብልፅግና እውን ለማድረግ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ስብሰባው ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን አመራሮቹ የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባቀረበው ሰነድ ውይይት ያካሂዳሉ፡፡

በሰነዱ ላይ ገለጻ ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ ብልፅግና ፓርቲ /ቤት ሃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ በህብረ ብሄራዊ አገራዊ ፓርቲ ምስረታ፣ አጣብቂኝ ላይ የወደቀውን ሀገራዊ ኢኮኖሚ በመታደግ ልማትና እድገትን በማስቀጠል፣ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና አንድነት በማስከበርና በሌሎችም መስኮች የተመዘገቡ ድሎችን አብራርተዋል፡፡

በዚህ ሂደት ያጋጠሙ ችግሮችን ለመቅረፍ በአመራሩና አባላት ውስጥ የአመለካከትና የተግባር አንድነት የሚያጎለብቱ፤ ህዝቦችን የሚያቀራርቡና ትስስርን የሚያጠናክሩ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

Share this Post