ባለስልጣኑ ለሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን አመራሮችና ባለሙያዎች የተፋሰስ ልማት ስራዎችን አስጎበኘ፡፡

የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የውሃ መገኛ በሆነው የለገዳዲ ግድብ ዙሪያ እየተሰሩ ያሉ የአከባቢ ጥበቃ እና ተፋሰስ ልማት ስራዎችን እንዲሁም የንፁህ ውሃ ማጣራት ሂደትን ለጋዜጠኞች እና የኮሙዩኒኬሽን አመራሮችና ባለሙያዎች አስጎብኝቷል፡፡

በጉብኝቱ ላይ የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ / ዘሪሁን አባተ ከዚህ በፊት ለተፋሰስ ልማት ስራዎች ትኩረት ተሠጥቶ ባለመሰራቱ ግድቦች በደለል እየተሞሉ ውሃ የመያዝ አቅማቸው እየቀነሰ እንደመጣ እና ውሃውን ለማጣራት የኬሚካል ፍጆታ እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋለ፡፡

ይህንኑ በመገንዘብ ባለስልጣኑ ከባለፈው ሦስት አመት ወዲህ የአከባቢው አርሶ አደሮችን በማሳተፍ ብሎም ቪተንስ ኢቪደስ ኢንተርናሽናል ከተባለ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ጋር በመተባበር 1 ሺህ 32 ሄክታር መሬት ላይ የተፋሰስ ልማት ስራዎችን ለመሠራት ዕቅድ ተይዞ እስካሁን 229 ሄክታር ላይ መሰራቱን አብራርተዋል፡፡

ያለ አከባቢ ጥበቃ የንፁህ ውሃ ምርት አይታሰብም ያሉት የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ በግድቦች ዙሪያ የከተማ መስፋፋት እና አዳዲስ ሰፈራዎች መኖር ከውሃ ምርት ጥራት አንፃር ስጋት አሳድሮብናል ብለዋል፡፡

ለሚዲያዎች ግንዛቤ ማስጨበጥ በርካቶችን ተደራሽ ለመሆን የሚያግዝ በመሆኑ ከተለያዩ የቴሌቪዥን፣ ራዲዮና ህትመት ሚዲያዎች እንዲሁም ለከተማው የኮሙኒኬሽን ቢሮ አመራር እና ባለሙያዎች የባለስልጣኑን አጠቃላይ የስራ እንቅስቃሴ በኢግዚብሽን በማቅረብና ውይይት በማድረግ ማሳወቅ ተችሏል፡፡

በጉብኝቱ ላይ የተሳተፉ የሚዲያ አካላትም ጉብኝቱ የተሸለ መረዳትን እንደፈጠረላቸው ገልጸው፤ በቀጣይ በስራቸው የተሻለ ግንዛቤ ለመፍጠር እንደሚሰሩም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

 

Share this Post