ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እና የአዲስ አበባ ኮሙኒኬሽን ቢሮ የስልጠና ስምምነት ተፈራረሙ

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እና የአዲስ አበባ ኮሙኒኬሽን ቢሮ የስልጠና ስምምነት ተፈራረሙ

 

ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አክሲዮን ማህበር በአዲስ አበባ ከተማ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ስር ለሚገኙ 500 በላይ ለሚሆኑ አመራሮች እና ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና ለመስጠት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራረመ፡፡

ስምምነቱን የተፈራረሙት የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አድማሱ ዳምጠው እና የአዲስ አበባ ከተማ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ዮናስ ዘውዴ ናቸው፡፡

የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አድማሱ ዳምጠው በፊርማ ሥነ ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ የፋና የስልጠና ማዕከል የሚሰራቸው ስራዎች እውቀት ላይ የተመሰረቱ መሆናቸውን ገልጸው፥ የሚዲያ ስራዎች እውቀትንና እውነትን መሰረት ያደረጉ መሆን እንዳለባቸውም አመላክተዋል።

ከዚህ አኳያ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያለውን ሰፊ የስልጠና አቅም ተደራሽ ለማድረግ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመተባበር እንደሚሰራ ሁሉ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮሙኒኬሽን ቢሮ ጋር ለመስራት ይህንን ስምምነት መፈራረሙ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቁመው፥ ስልጠናው ሙያተኛው የበለጠ እውቀትና ልምድ ላይ የተመሰረተ ስራ እንዲሰራ ለማድረግ የሚያስችል በመሆኑ ስምምነቱን በሙሉ ኃላፊነት የምንተገብረው ይሆናል ብለዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ዮናስ ዘውዴ በበኩላቸው፥ ከዚህ በፊት በተለምዶና በልምድ ሲሰሩ ከነበሩ አሰራሮች ወጣ ብሎ፥ ሳይንስን መሰረት ያደረጉና ልምድንም ግምት ውሰጥ ያሰገቡ የኮሙኒኬሽን መንገዶችና እሳቤዎች መሳለጥ አለባቸው ከሚል ብርቱ አሳብ የተነሳ ይህንን ውል ልንፈራረም ችለናል ነው ያሉት።

አያይዘውም አገራችን የጀመረችውና እያለፍንበት ያለው የሪፎርም አስተሳሰብና አመለካከት ከዳር እንዲደርስ ሙያና ሙያተኛ መገናኘት ሲችል ብቻ ነው ያሉት አቶ ዮናስ፥ ይህንንም ለመተግበር ከተማችን የሚያስፈልጋት የኮሙኒኬሽን ባለሙያ የሰለጠነ፣ ዓለማችን የደረሰችበትን ቴክኖሎጂ በእውቀትና በብቃት የሚጠቀም መሆን አለበት ብለን ስለምናምን ነው ይህንን የስልጠና ውል ስምምነት የተፈራረምነው ብለዋል።

የስልጠና ስምምነቱ የአዲስ አበባ ኮሙኒኬሽን ቢሮ እስከ ወረዳ ድረስ በመዋቅሩ ስር ለሚገኙ የህዝብ ግንኙነትና የኮሙኒኬሽን አመራሮች እና ባለሙያዎች ስራቸውን በብቃት እንዲወጡ የሚያግዝ መሆኑ ተገልጿል፡፡

Share this Post