ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በቂርቆስ ክ/ከተማ ዘርፈ ብዙ በአጭር ጊዜ የሚከናወኑ ሰው ተኮር የልማት ፕሮጀክቶችን ግንባታን በይፋ አስጀመሩ፡፡

 

የቂርቆስ ክ/ከተማ የከተማው ማእከል ሲሆን በርካታ በዝቅተኛ ኑሮ የሚገኝ ማህበረሰብ የሚገኝበት ክ/ከተማ ነው፡፡

እነሆ ዛሬ ክ/ከተማው በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚከናወኑ ለሌላው የከተማው አካባቢዎች ተሞክሮ መሆን የሚችሉ አንገብጋቢ የህዝብ ጥያቄ ባለባቸው ስድስት ዋና ዋና ዘርፎች የልማት ፕሮጀክቶችን ይፋ አድርጓል፡፡ ከነዚህም ውስጥ ፡-የቤት አቅርቦት ፤ የዳቦ አቅርቦት ማሻሻልና ማእድ ማጋራት ፤የከተማ ግብርና፤የከተማ ፅዳትና ውበት ፤የአገልግሎት ማሻሻል፤ የእሁድ ገበያ ማስፋፋት ይገኙበታል፡፡

የቤት ፕሮጀክቶቹ በተለይም ከነበረው ያረጁ ቤቶች እድሳት በተጨማሪ የአዳዲስ ቤቶች ግንባታ ህብረተሰቡ ከአካባቢውና ማህበራዊ ህይወቱን ከመሰረተበት አካባቢ ሳይፈናቀል በ2 ወራት ውስጥ የሚጠናቀቅ የዝቅተኛ ማህበረሰብ የኑሮ ደረጃ የሚመጥን ዋጋ ያለው (Affordable house) እና ዛሬ የተጀመሩት 4 የጋራ መኖርያ ቤቶች በአጠቃላይ እስከ 200 ቤቶች የሚይዝ ግንባታ ነው፡፡ይህም ከከተማው እድገት ጋር የሚጣጣም እና ከግል ሴክተሩ ጋር በመተባበር የሚተገበር የG+9 አዲስ አይነት የተገጣጣሚ ቤቶች ነው፡፡

በሁለተኛ ደረጃ በተለያዩ አካባቢዎች 8 የዳቦ ፋብሪካዎችን በተመሳሳይ ከባለሃብቶች ጋር በመተባበር የሚገነቡ ሲሆን 2 የምገባ ማእከላትን በቀን አንድ ጊዜ መመገብ የማይችሉ ዜጎች የሚመገቡባቸው እና 32 የሸገር ዳቦ ማቅረቢያ ቦታዎች በይፋ ግንባታ በይፋ ተጀምረዋል፡፡

በሌላ በኩል በክ/ከተማው የከተማ ግብርናን በስፋት በመተግበር በመሃል ከተማ የጓሮ አትክልት በ(vertical farming) መንገድ ሰዎች ራሳቸውን በምግብ የሚችሉበትን መንገድ በስምንት ሞዴል ቦታዎች የሚተገበር ይሆናል፡፡

በተጨማሪም በክ/ከተማው ለመላው የአዲስ አበባ ሞዴል የሚሆን ከተማውን ውበት የሚጠብቀውን ቡራቡሬ የሆነውን የህንፃ ቀለም በማስተካከል ለከተማው የሚሆን ተመሳሳይ ብራንድ ቀለም በመፍጠር አዲስ አበባ እንደ ስሟ አዲስና ውብ እንድትሆን የሚያስችል ሞዴል ስራ ነው፡፡

በእነዚህ ፕሮጀክቶች ማስጀመርያ ላይ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ እንደተናገሩት በነዚህ ፕሮጀክቶች ከተማዋ የሚገባትን እድገት እንድታገኝና በዚህ በእድገትና ለውጥ ውስጥ ደግሞ የዜጎች ህይወት አብሮ የሚቀየርበት ስራዎች ናቸው ብለዋል፡፡

እንደ ክብርት ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አገላለፅ እነዚህ ስራዎች ያከበረንን ህዝብ መልሰን የምናከብርበት በድምፁ የመረጠንን ህዝብ የምንክስበት ነው ያሉ ሲሆን በተለይ ከቤቶች ግንባታ አንፃር የከተማው ነዋሪ ሌላው ቢቀር የመኖርያ ቤት ባለቤት መሆን እንኳን ባይችል ተከራይቶ መኖር የሚችልባት ከተማ ማድረግ አለብን ሲሉ ገልፀዋል፡፡

ለከተማው ነዋሪ በፅዱ አካባቢ መኖር ቅንጦት አይደለም ያሉት ከንቲባ አዳነች ዜጎች በንፁህና ያማረ አካባቢ መኖር መብታቸውም ጭምር ነው ብለዋል፡፡ስለሆነም ነዋሪው እነዚህ ፕሮጀክቶች እንዲሳኩ አብሮ በመስራት በጋራ በመንቀሳቀስ ለስኬቱ እንዲረባረብም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብና አዲስ እናደርጋለን!!

#እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ

#ከተማችንን በጋራ እናልማ

#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

Share this Post