የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮሙኒኬሽን ቢሮ ም/ሀላፊ አቶ ሁሴን ዝናቡ እንደተናገሩት ወጣቶች ሰላምን ዘርቶ ሰላምን ለማጨድ እና ሰላምን ለመመገብ በማህበራዊ ሚዲያው ከእኔነት ይልቅ እኛነትን በማጉላት አብሮነትን ማጠናከር እንደሚገባ አስረድተዋል።
ወጣቶች ማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀማቸው ለከተማችንና ለአገራችን ሰላም እና እድገት እሴት በሚጨምሩ ጉዳዮች ላይ ማዋል እንደሚገባቸው የጠቆሙት አቶ ሁሴን በከተማችን በፍጥነትና በጥራት እየተገነቡ የሚገኙ ሜጋ ፕሮጀክቶች ተሞክሮ በአገር ደረጃ እንዲስፋፋም ወጣቶች የበኩላቸውን እንዲወጡ አስገንዝበዋል።
የአዲስ አበባ ወጣቶች አደረጃጀት ሃላፊ ወጣት መለሰ አባተ ማህበራዊ ሚዲያን ለአገር ግንባታ የተጠቀሙ አገሮች ለዕድገታቸው አጋዢ እንደሆነላቸው ጠቁመው በተቃራኒው ማህበራዊ ሚዲያውን አለአግባብ የተጠቀሙ ግለሰቦችና ቡድኖች የተበራከቱባቸው አገራት እስከ መፈራረስ ስለደረሱ ትምህርት ወስዶ አጠቃቀምን መግራት እንደሚገባ አብራርተዋል።
ስልጠናውን የሰጡት የሚዲያ አማካሪ አቶ ዓብይ ሰለሞን የዘመኑ ቴክኖሎጂ ሁሉም ሰው በፅሁፍም ሆነ በተንቀሳቃሽ ምስል መረጃዎችን የሚያስተላልፍበትን ዕድል ስለፈጠረ ትክክለኛ መረጃዎችን ተደራሽ ለማድረግ እና የተሳሳቱትን ለማረም የማህበራዊ ሚዲያ ፕላትፎርሞችን እንደየዝንባሌአቸው በአግባቡ ሊጠቀሙባቸው እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ስልጠናው ማህበራዊ ሚዲያን በተመለከተ ያላቸውን እውቀት እና ክህሎት እንዳጎለበተላቸው የገለፁት የስልጠናው ተሳታፊ ወጣቶች የከተማ አስተዳደሩ አዲስ አበባን የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ የጀማመራቸው ውጥኖች በሁሉም መስክ ፍሬአማ እንዲሆኑ የድርሻቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።