የአዳዲሶቹ የዳቦ ማከፋፈያ፣ የአትክልትና ሌሎች መሸጫ ሱቆች ለከተማዋ ስጦታ ናቸው!!

 

በክብርት ከንቲባ ልዩ ድጋፍ እየተሰጣቸው የሚገኙ የልደታና ቂርቆስ ክ/ከተማዎች ላይ በ60 ቀናት ፕሮጀክቶች እየተሰሩ ያሉት የዳቦ መሸጫ ሱቆች በከተማችን አዲስ ገፅታን የሚያላብሱ በውበት ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚም በማህበራዊም እንዲሁም በአካባቢ ጥበቃም (enviromental sustainability) እጅግ ጠቀሜታ ያለው ስራ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት 5 የሸገር ዳቦ ማከፋፈያና የአትክልት መሸጫ ሱቆች የሙከራ ስራ የጀመሩ ሲሆን በያዝነው ወር መጨረሻ 20 የሚሆኑ ተጨማሪ የማከፋፈያ ማዕከላት ስራ ለመጀመር ዝግጅት ተጠናቆላቸዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በአንድ የሸገር አውቶቡስ ለአንድ ማህበራት የስራ እድል ሲፈጥር የነበረ በአሁኑ ወቅት ለሁለትና ከዛ በላይ ማህበራት በአንድ የኮንቴይነር መሸጫ ቦታ የስራ እድል ይፈጠርላቸዋል፡፡

ከዚህ በፊት የሸገር ማከፋፈያ ሆነው አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ የከተማ ባሶች ጊዜያዊ መፍትሄ የነበሩ ሲሆን በሂደትም ከማርጀታቸውም በተጨማሪ አቀማመጣቸው ብዙ ቅሬታ ይነሳበት የነበረ ፣ ከዳቦ ማከፋፈል ውጪ ተጨማሪ አገልግሎቶችን ሙሉ ቀን የማይሰጡና፤ አንዳንድ ቦታዎችም የእግረኛ መንገዶችኝ በመዝጋት ጭምር ለትራፊክ አደጋዎች የሚያጋልጡ ነበሩ፡፡

አሁን ግን በከንቲባ አዳነች አቤቤ ልዩ ክትትል በሚደረግባቸው ሁለቱ ክ/ከተሞች (ልደታና ቂርቆስ) የተጀመሩት የዳቦ መሸጫ ኮንቴይነሮች Upcycling (አልቆ መጠቀም) ስልትን በመከተል የጭነት አገልግሎት ጊዜያቸው ያበቃላቸውን ኮንቴይነሮች ከመጣል ይልቅ በልዩ መልክ አድሶ ወደ ስራ በማስገባት የሚከናወን ነው፡፡ ኮንቴነሮቹ የሚደረግላቸው እድሳት ምቹና ዘመናዊ እንዲሆኑ ያደረገና በፀሃይ ብርሃን መብራትን ማመንጨት እንዲችሉ ተደርጎ የሚሰራም ነው።በዚህም ኮንቴይነሩ በስራ ላይ ሲውል ለበርካታ ዜጎች ተጨማሪ የስራ እድል ከመፍጠሩም ባሻገር ቀድሞ ይሰጥ ከነበረው አገልግሎት በይዘትና ጥራት በተሻለ በመስራት በከተማችን ዝቅተኛው የህብረተሰብ ክፍል የሚያገኘውን አገልግሎት በገፃታ፣ በጥራትና በንፅህና ለማቅረብ የሚያስችል ነው። ዜጎች እለታዊ ዳቦን ከማከፋፈያ ማዕከላት ከመውሰድ በተጨማሪ እንደ ልዩ የህብረተሰብ ማዘውተሪያ ስፍራነትም የሚያገለግል ነው።

Up cycling (አልቆ መጠቀም) ከrecycling (ከመልሶ መጠቀም) ስልት ወጪን ከመቆጠብ ፤ የአካባቢ ብክለትን ከመከላከል እንዲሁም የከተማውን ገፅታ ከማሻሻል ረገድ ተመራጭ የሆነና አለማችን እየተጓዘችበት ካለው የዘላቂ ልማት ግብን የማሳካት ስራዎች እንደማሳያነትም የሚሆን አበረታች ስራ ነው።እነኚህ ውብ የዳቦ ማከፋፈያ ቦታዎች አልቀው ወደ ተግባር የገቡ ሞዴል ስራዎች ናቸው፡፡

Share this Post