ማህበራዊ ዕሴቶቻችን ለሰላም እና ለአገር ግንባታ ያለቸውን ፋይዳ በሚመለከት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከሁሉም የማህበረሰብ ተወካዎች ጋር የፓናል ውይይት አካሄደ

ማህበራዊ ዕሴቶቻችን ለሰላም እና ለአገር ግንባታ ያለቸውን ፋይዳ በሚመለከት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር

ከሁሉም የማህበረሰብ ተወካዎች ጋር የፓናል ውይይት አካሄደ

ማህበራዊ ዕሴቶቻችን ለሰላም እና ለአገር ግንባታ ያለቸውን ፋይዳ ጨምሮ አሁን የሚገኙበትን ወቅታዊ አቋም እንዲሁም በተሻለ ተጠብቀው ለትውልድ በሚተላለፉበት አስቻይ ሁኔታን በሚመለከት ጥናታዊ ፅሁፍ ቀርቦ ውጤታማ ውይይት ተካሂዶበታል ።

የማህበራዊ ዕሴት ግንባታን በሚመለከት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከከተማው አመራር አካዳሚ ጋር በጋራ ባዘጋጀው የፓናል ውይይት ላይ የኃይማኖት አባቶች ፣የአገር ሽማግሌዎች፣ሙሁራን ፣ሴቶች ፣ወጣቶች ፣የሁሉም የማህበረሰብ ተወካዮችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተው ማሄበራዊ እሴቶቻችንን አጽንተን ለመጠበቅ የሚያስችሉ ሃሳቦችን በማንሳት ከተሰብሳቢዎች ጋር ውይይት አድርገዋል።

በፓናል ውይይቱ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሁሴን ዝናብ ማህበራዊ እሴቶች የሕዝቦችን ማህበራዊ ግንኙነት በማጠናከር እርቅ ፣ፍትህና ርትዕ እንዲኖር ለማስቻል የጎላ አስተዋጽኦ ያላቸው በመሆኑ ሁላችንም በየደረጃው በተገኘንበት ሁሉ የየድርሻችንን ኃላፊነት መወጣት ይኖርብናል ብለዋል ።

እኛ ኢትዮጵያውያን ቱባ ማህበራዊ እሴቶችና ባህሎች ያሉን በፍጹም ላንለያይ በወንድማማችነት የተቆራኘንና የተሰናሰልን ህዝቦች ነን ያሉት ምክትል ኃላፊው የቆየውን ኢትዮጵያዊ ማሕበራዊ እሴታችንን ለመናድ ና ለመሸርሸር ከውስጥና ከውጭ በርካታ ሙከራዎች በተደጋጋሚ መልካቸውን እየቀያየሩ እየተፈጸሙብን ቢሆንም በወንድማማችነት እና በአንድነት አሸንፈን ዛሬም በጋራ በወንድማማችነት መቆም ችለናል ብለዋል ።

የአገራችንን ሁለንተናዊ ዕድገትና ብልጽግና በሚፈለገው ደረጃ ለማፋጠን እኔነትን በመተው እኛነትን ማስፈንና ማንገስ ይኖርብናል ሲሉ አጽንኦት ሰጥተው አቶ ሁሴን ተናግረዋል ።

ማህበራዊ እሴቶቻችን በልዩ ልዩ ጫናዎች እንዳይሸረሸሩ ሁሉችንም በየደረጃው በተገኘንበት ሁሉ ማህበራዊ ኃላፊነታችንን በቡድንም ይሁን በተናጠል ለመወጣት ዘውትር በዝግጁነት ልንቀሳቀስ ይገባል ሲሉ ገልጸዋል ምክትል ኃላፊው።

በፓናል ውይይቱ ላይ የአገር ሽማግሌዎችና የፓናል ውይይቱ ተሳታፊዎች እንደተናገሩት መንግሥትን ጨምሮ የአገር ሽማግሌዎችና የኃይማኖት ተቋማት የወጣቶች የስብዕና ግንባታ እና ለዘመናት የዘለቀውን በአብሮነትና በወንድማማችነት ተከባብሮ የመኖር ማህበራዊ እሴታችንን ማበልጸግን በሚመለከት ሁሉችንም በኃላፊነት የድርሻችንን መወጣት ይኖርብናል ሲሉ አሳስበዋል ።

የአዲስ አበባ ሥራ አመራር አካዳሚ ኃላፊ ዶ/ር ደሳለኝ ፔጥሮስ በበኩላቸው አጠቃላይ የመንግስትና ልዩ ልዩ ማሕበራዊ መዋቅሮች ማንኛውንም አገልግሎት ለዜጎች ሰውነትን ብቻ ባስቀደመ መልኩ አገልግሎት መስጠት እንደሚጠበቅባቸው ጠቅሰው የኃይማኖት ተቋማትና የአገር ሽማግሌዎች በወጣቶች የስብዕና ግንባታና የማሕበራዊ እሴቶቻችን መበልፀግ ላይ ከሚመለከታቸው ሁሉ አገራዊ አንድነታችንን ለማጽናናት በሚያስችል መልኩ አበክረው ልሰሩ ይገባል ብለዋል ።

Share this Post