"ሃገራችን በጀግኖች ልጆቿ ብቻ ሳይሆን በፈጣሪ ሃይልም በኪዳን የቆመች ስለሆነች ፤ ሃገራችንን ማፍረስ አይችሉም!!"

 

ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ

የየካ ክ/ከተማ በ60/90 ቀናት ሲያስገነባቸው የቆያቸው ከ818 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው የተለያዩ ሰው ተኮር ፕሮጀክቶች በዛሬው እለት አስመርቋል፡፡

ፕሮጀክቶቹ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነ ልዩ ድጋፍና ክትትል ሲረግባቸው የቆዩና በበጎ ፍቃደኞች ፤በህዝብና በመንግስት ተገንብተው የተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡

ከተመረቁት መሃከል የዳቦ ፋብሪካ፤ የዳቦ እና አትክልት መሸጫ ሱቆች፤ የምገባ ማእከላት ፤እንዲሁም አዳዲስ ዘመናዊ የመኖርያ ቤት ግንባታ፤ 389 የአቅመ ደከማ ወገኖች የመኖርያ ቤት እድሳት ፤የጓሮ አትክልት ልማት የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡

በዚህ ስነስርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ እንደገለፁት ከሃምሌ መጀመርያ ጀምረን እስካሁን ድረስ ፕሮጀክቶችን እየመረቅን እንገኛለን ያሉ ሲሆን ፤ ፕሮጀክት በፍጥነት ጀምረን መጨረሳችን የሚያናድዳቸው በሃገራችን ላይ ጦርነት በመክፈት የጀመርነውን ጉዞ ሊያስቆሙን የሚሞክሩ እያሉ መመረቃችንን ቀጥለናል ብለዋል፡፡

እኛ እንዲህ እንድንሰራ በአሁን ሰአት በጦርነት ቦታ ላይ የህይወት ዋጋ እየከፈሉ ያሉ ጀግና መከላከያ ሰራዊት አባላት ክብር እንሰጣን ሲሉም ከንቲባ አዳነች ለመከላከያ ሰራዊቱ ክብር አሳይተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ሃገራችን ለሰላም እጅዋ ተዘርግቷል፤ ያሉት ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አገራችን ግጭት ሰልችቷታል፤ ጦርነት ታወግዛለች ፤በፍፁም ወደ እርስ በእርስ ጦርነት መግባት አንፈልግም ፤ግድ ሆኖ ከመጡብን ግን እንደሁልጊዜውም ራሳችንን እከላከላለን በማለት ገልፀዋል፡፡

ሃገራችን በጀግኖች ልጆቿ ብቻ ሳይሆን በፈጣሪ ሃይልም፤ በኪዳን የቆመች ሃገር ስለሆነች፤ ሃገራችንን ማፍረስ አይችሉም ሲሉ አክለዋል፡፡

በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነን በዚህ አመት ወደ 20 ቢሊዮን ብር ያህል ከመንግስት ወጪ ያደረግንባቸው ፤ ወደ 300 የሚሆኑ በተለያየ ህብረተሰብ ተሳትፎ ደግሞ ከ300 በላይ ፕሮጀክቶችን መርቀናል ሲሉም ገልፀዋል፡፡

ከዚህ የምንማረው ከተሳሰብን አብረን ከቆምን ፤ሁላችንም የምንችለውን ጡብ ካስቀመጥን ፕሮጀክት ገንብተን በፍጥነት እንጨርሳለን፤ ፕሮጀክት ስንሰራ ሃገር እየገነባን እንደሆነ እናምናለን፤ ሲሉም ገልፀዋል፡፡

አቅማችንን እናስተባበር፤ አእምሯችንን እናሰባስብ ፤ እንደማመጥ፤ ሰከን እበል፤ ይሄንን ካደረግን የሚስቆመን ሃይል የለም ብለዋል፡፡

በምክትል ከንቲባ ማእረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነ በበኩላቸው ዛሬ የሰራናቸው ስራዎች ከፕሮጀክት በላይ ናቸው ያሉ ሲሆን በተለይም የብዙዎችን ህይወት የሚቀይሩ በተለይ በልቶ ማደር የማይችሉትን ማህበረሰብ ጭምር ያስታወሱ ናቸው ብለዋል፡፡

የምንገናኘው በምርጫ ወቅት ብቻ አይደለም ያሉ ሲሆን በምርጫ ቃል የገባነውን አሁን ወደ ውጤት ለመቀየር ስምንት ሰዓት ብቻ ሳይሆን ተጨማሪ ሰዓት በመስራት ፤ ጭምር ነው ፤ ይህ ግን መነሻችን እንጂ መጨረሻችን አይደለም ብለዋል፡፡

Share this Post