አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለፉት ሶስት ወራት በተደራጀ የህዝብ ተሳትፎ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን በተቀናጀና በተናበበ መንገድ አከናውኗል፡፡

 

የከተማ አስተዳደሩ ባለፉት ሶስት ወራት በተደራጀና የዝግጅት ምእራፍ ስራዎችና የቀጣይ ትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ከወረዳ ጀምሮ እስከ ከተማ ድረስ ያሉ የከተማው ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ውይይት አካሂደዋል፡፡

በውይይቱም ባለፉት ሶስት ወራት ተደራራቢ ተግባራትን አመራሩ በትብብርና በቅንጅት ማሳካት መቻሉንና ውጤት ማስመዝገቡም ተገልጧል፡፡

ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በውይይቱ ማጠቃለያ እንደተናገሩት ከሁሉ በላይ በተደራጀ በተናበበ ሁኔታ ከመራን ስራዎቻችን ስኬታማ እንደሚሆኑ ልምድ የወሰድንበት ነው ሲሉ ገልፀዋል፡፡

አመራሩ ራሱ ግንኙነቱ ጤናማ ከሆነ ህዝብ ውስጥ ያለውም ሁኔታ ጤናማ እንደሚሆን ያየንበትም ነው ብለዋል፡፡

እንደ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አስተዳደሩ ባለፉት ሶስት ወራት በክረምት በጎ ፍቃድ ስራዎች በምገባና ማእድ ማጋራት ፤በመሳሰሉት ድሃውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎች የተከናወነባቸው መሆኑን አንስተዋል።

በወሰን ማካለል ስራ የህዝቦችን ዘላቂ ግንኙነት በሚያጠናክር መልኩ የተሰሩት ስራዎች ለዘላቂ ሰላማችን እጅግ ጠቃሚ እንደነበር ተነስቷል፡፡በተጨማሪም በህግ ማስከበርም ጠንካራ ሰራ መሰራቱን አስታውሰዋል፡፡

በተለይ አሸባሪዎች በከተማችን የኢኮኖሚ አንድ ግንባር በማድረግ ለይተው የኑሮ ውድነቱን ለማባባስ ያደረጉትን ጥረት የከሸፈበት በርካታ ምርቶችን ወደ ከተማዋ የማስገባት ስራ በጥንካሬ የሚነሳ መሆኑ ተቀምጧል፡፡

እንደ ከንቲባ አዳነች አጠቃላይ ትምህርት የሚወሰድባቸውና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ የሆኑት ነጥቦች ተቋም ግንባታ ስራ ፤የተደራጀ የህዝብ ተሳትፎ ማጠናከር ፤የተጠያቂነትን ስርዓት ማስፈን (የፖለቲካ ተጠያቂነት ብቻ ሳይሆን ህጋዊ ተጠያቂነት ማስፈን ያስፈልጋል) ፤በቅንጅት መስራት፤ የስራ ባህል ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን አስምረውበታል፡፡

አገልግሎት ከእጅ መንሻ ነፃ መሆን አለበት ያሉት ከንቲባዋ የጠላትን እቅድ ማፈራረስ የቻለ አመራር እንዴት አገልግሎትን ነፃ ማድረግ ይሳነዋል በሚል ጠይቀዋል፡፡በቀጣይ የትኩረት መስክ ብለው ከንቲባ አዳነች ያስቀመጡት ጠንካራ ፓርቲ ለጠንካራ መንግስት

በዚህም ተቋማትም የመፍጠር ስራ፤ አደረጃጀቶችን የማጠናከር በተደራጀ የትግል ስልት ስራችን የመምራት ሁኔታ የሚያጠቃልል መሆኑን አንስተዋል፡፡

ዲጂታላይዜሽን የከተማዋ ቀጣይ የትኩረት መስክ መሆኑንም ከንቲባ አዳነች አንስተዋል፡፡

እንዲሁም የህግ በላይነትንና ዘላቂ ሰላም የማረጋገጥ ስራም በትኩረት የሚሰራ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ብልፅግና ፓርቲ ፅ/ቤት ሃላፊ አቶ መለሰ አለሙ በበኩላቸው ያለፍንበትን ሁኔታ ሰላም ስለሆነ ብቻ አቅልለን ልንመለከተው አይገባም ብለዋል፡፡ዋናው የአአምሮ ዝግጁነት ነው ያሉት አቶ መለሰ አሁን ያለው የስነልቦና ጦርነቱን ለመወጣት ዛሬ ቢደክመውም ስለነገ የሚያስብ አመራር ያስፈልጋል ብለዋል አሁንም ቢሆን የህዝቡ የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄ ፍላጎት ጊዜ የሚሰጥ አይደለም ያሉት አቶ መለሰ የስኬት ግምገማችን ከህዝቡ ፍላጎት ጋር የሚጣጣም መሆን አለበትም ብለዋል::

የአዲስ አበባ ከተማ ም/ከንቲባ አቶ ጃንጥራር አባይ በተጨማሪም እንዳነሱት የአመራሩ የስራ ባህልና ተቋም ግንባታ ወሳኝ መሆኑን ገልፀው፤ የአመራር ህብረት ያለው ለውጤት የሚተጋ አመራር በመኖሩ ብዙ ችግሮችን አልፈናል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ሰው በዓል ሲመጣ መጣልኝ ብሎ የሚደሰትበት እንጂ መጣብኝ ብሎ የሚጨነቅበት እንዳይሆን መስራት አለብን ሲሉም ገልፀዋል፡፡

Share this Post