የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በዋሽንግተን ዲሲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በመገኘት በአሜሪካ ዲ ኤም ቪ እና አካባቢዉ የሚገኙ በኢንቨስትመንት እና ቢዝነስ የስራ መስኮች ላይ ከተሰማሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትዉልደ ኢትዮጵያዊያን የዳያስፖራ አባላት ጋር ውይይት አድርገዋል
ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ October 26/2022 በዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘዉ የኢፌዴሪ ኤምባሲ የዲያስፖራ አባላቱን ባወያዮበት ወቅት የዲያስፖራ አባላቱ አዲስ አበባ ከተማ በብራዚል ሪዮ ዲጄኔሮ የ2022 ሚላን ፓክት አዋርድ እና በአርጀንቲና ቦነስ አይረስ በተካሄደዉ የC40 የአለም ከተሞች ስላሸነፈችው ሽልማት የተሰማቸዉን ኩራትና ደስታ ገልፀዋል።
ከንቲባ አዳነች እስክካሁን በተገኙ ድሎችም ሆነ ፈተናዎችን ለመሻገር በሚደረገዉ እንቅስቃሴ ዉስጥ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ሚና ወደር የለሽ እንደሆነም አንስተዋል። አሁንም አዲስ አበባን ከዲፕሎማቲክ ማእከልነቷ ባሻገር ለነዋሪዎቿ ምቹ የሆነችና እንደ ስሟ አበባ ለማድረግ በሚያደርገው ጥረት: በኢንቨስትመንት፤ በመኖርያ ቤት ግንባታ: በንግድ ፤ በሳይንስና ቴክኖሎጂ፤ በእውቀት ሽግግር ፤ የከተማዋን የጤና ቱሪዝም ማእከልነት እቅድ በማሳካት ፤ ተሳትፎ እንዲያደርጉ በከንቲባ አዳነች አቤቤ ጥሪ ቀርቦላቸዋል፡፡
የዲያስፖራ አባላቱም በሀገራቸው እየተካሄደ ባለው አጠቃላይ እንቅስቃሴና እየመጣ ባለው ለውጥ ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀው የከንቲባዋን ጥሪ መቀበላቸውና በሃገር ጉዳይ በንቃት መሳተፍ እንደሚፈልጉ አሳውቀዋል። ሆኖም ወደ ሀገር ሲመጡ የሚያጋጥማቸውን የቢሮክራሲ ችግሮች መንግስት እንዲቀረፍላቸው ጠይቀዋል፡፡
ከንቲባ አዳነችም ይህንን ችግር ለመፍታት ዋነኛው መፍትሄ ስርዓት (system) መገንባት እና ማጠናከር እንዳለበት ገልፀው ይህንን ማድረግ የመንግስት የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በዚህ ዙርያም ዲያስፖራው በተለይ በቴክኖሎጂ አገልግሎትን ለማዘመን የሚደረገውን ጥረት እንዲደግፍ አሳስበዋል፡፡