ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ
የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽን የከተማይቱን ሁለንተናዊ ሰላም በማስጠበቅ የተለያዩ የሽብር ድርጊቶችን በመከላከል እና በፖሊሳዊ አገልግሎት የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የሰራዊቱ አመራሮችና አባላት ዕውቅናና ማበረታቻ ስነስርዓት አከናወነ፡፡
በዕውቅናና ሽልማት መረሀ-ግብሩ ላይ ኢትዮጵያ ጸንታ የቆመችው ሕይወታቸውን ሳይሰስቱ የሚሰጡላት ጀግኖች ልጆች ስላሏት ነው ያሉት ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የኢትዮጵያን ቀጣይነት ሁሌም በጀግኖች ልጆቿ ውስጥ እንመለከታለን ብለዋል።
ፖሊስ በቴክኖሎጂና በአደረጃጀት እንዲሁም ተደራሽነቱን በሚፈለገው አግባብ እያሰፋ እንዲሄድ ዘርፈ ብዙ ጥረት እያደረግን እንገኛለን ያሉት ከንቲባዋ ይህም በሁሉም ረገድ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ ተናግረዋል።
ጠላቶቻችን በጦር ግንባር ያጋጠማቸውን ኪሳራ አዲስ አበባ ላይ ለማካካስ ያደረጉትን ጥረት በማክሸፋችሁ የአዳስ አበባ ፖሊስ አመራሮችና አባላት ለከፈላችሁት ዋጋ ሁሉ ይህ ዕውቅናና ምስጋና ይገባችኋል ሲሉ አስመረው ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮምሺን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው በበኩላቸው የአዲስ አበባ ፖሊስ ከመላው የጸጥታ ተቋማት ጋር በቅንጅት ከለውጡ ማግስት አንስቶ ትህነግና ተላላኪዎቹ አዲስ አበባን የጥፋት አጀንዳቸው መነሻና መድረሻ ለማድረግ ተቀጣጣጣይ ፈንጂዎችን ጭምሮ ልዩ ልዩ ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያዎችን በማዘዋወር እንቅስቃሴ ያደረጉ ቢሆንም ሕዝባችንን ያሳተፈ ጠንካራ የመረጃ ልውውጥ ስርዓት በመዘርጋት በቁጥጥር ስር እያዋልን ከተማችንን በሁለንተናዊ መልኩ ሰላም ማድረግ ችለናል ብለዋል።
በዝግጅቱ ላይ የፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮምሽነር ጀነራል መላኩ ፈንታ እና ሌሎች የፌደራልና የከተማዋ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል፡፡