በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተፈረመውን የሰላም ስምምነት አስመልክቶ የወጣው የጋራ መግለጫ ነጥቦች ፦

 

1. ዘላቂ ግጭት ማቆምና ዘላቂ ሰላም ማምጣት በሚለው የስምምነቱ አንቀጽ 3 መሰረት የኢትዮጵያ መንግስትና የሕወሓት ተወካዮች ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለተቀረው ዓለም ከ10 ቀናት ካደረጉት ጥልቅ ድርድር በኋላ የሰላም ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ይፋ አድርገዋል።

2. በዘላቂነት የተኩስ ድምጽ እንዳይሰማና በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመት የቆየው ግጭት እንዲቋጭ ከስምምነት ላይ ደርሰናል።

3. ግጭቱ በአሳዛኝ ሁኔታ የበርካታ የዜጎች ሕይወት እንዲጠፋና መተዳደሪያ እንዲወድም አድርጓል። ስለሆነም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎትና ሕዝብ ጥቅም ሲባል የግጭት ምዕራፍን በመዝጋት በሰላምና በመግባባት ለመኖር ከመግባባት ላይ ደርሰናል።

4. የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት መጠበቅና የኢፌዴሪ ሕገ መንግስት ማክበርና መገዛት ቁርጠኛ መሆናችንን አረጋግጠናል፤

5. ከጉዳዩ መሰረታዊነት አኳያ ኢትዮጵያ ያላት አንድ መከላከያ ኃይል ብቻ ነው። በመሬት ላይ ያለውን የጸጥታ ሁኔታ ከግምት በማስገባት የሕወሓት ታጣቂዎች ሙሉ ለሙሉ ትጥቅ እንዲፈቱና መልሶ የሚዋሃዱበት ዝርዝር መርሐግብር ላይ ከስምምነት ደርሰናል።

6. የኢትዮጵያ መንግስት ከሰብአዊ እርዳታ ድርጅቶች ያለውን ትብብር በማጠናከር ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች በሙሉ የእርዳታ ተደራሽነት ማሳደግ እንደሚኖርበት ከመግባባት ላይ ደርሰናል።

7. በትግራይ ክልል ሕገ መንግስታዊ ስርዓት ወደ ነበረበት እንዲመለስ፣ የፖለቲካ ልዩነቶች የሚፈቱበት ማዕቀፍ ማዘጋጀት እንዲሁም ተጠያቂነት፣ሕጋዊነት፣እርቅና ቁስል መሻርን እንዲረጋጋጥ የሚያደርግ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ማዕቀፍ ማዘጋጀትን ያካተተ የሽግግር እርምጃዎች ለመውሰድ ተስማምተናል።

8. የተደረሰውን ስምምምነት ያለ ምንም መዘግየት እንዲፈጸም እናደርጋለን። ሁሉንም አይነት ግጭቶችና ግጭት ቀስቃሽ ፕሮፓጋንዳዎችን ለማቆም ተስማማምተናል። የስምምነቱን ተፈጻሚነት ብቻ የሚያሳልጡ መግለጫዎችን እናወጣለን። በገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ስምምነቱን እንዲፈጸም ድጋፍ እንዲያደርጉ፣ የጥላቻና መከፋፈል መልዕክቶችን እንዲያቆሙና ያሏቸውን ሀብቶች ለኢኮኖሚ ማገገሚያና ማህበራዊ ትስስር በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ እንዲያውሉ ጥሪ እናቀርባለን። ሲል ከኢቢሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

 

 

 

Share this Post