ከንቲባ አዳነች አቤቤ የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማን ሞዴል ክ/ከተማ ለማድረግ በሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ ከባለሀብቶች ጋር ውይይት አደረጉ።

የውይይቱ ዋና አላማም በክፍለ ከተማው በዘጠና ቀናት እቅድ ውስጥ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በፍጥነት መፍታት ፤ምቹ የስራ ቦታ መፍጠር ፤የአገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻል ፤በክ/ከተማው የልማት ስራዎችን ማፍጠን፤ የከተማ ግብርና ማስፋት፣ የገበያ ማረጋጋትና ሌሎች ሰው ተኮር የሆኑ ስራዎችን በተለየ ትኩረት በመፈፀም የኑሮ ውድነትን ተፅዕኖ መቀነስ በጎ ፍቃደኛ ባለሀብቶችንና አጋር አካላትን በማሳተፍ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ሊያደርጉ የሚችሉ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ ማድረግ በነዋሪዎችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ክፍለ ከተማውን ፅዱና ውብ አረንጓዴ እንዲሆን መስቻል እና የመተጋገዝና የመረዳዳት ባህልን እንዲጎልበት ማድረግ እንደሆነም ተገልጿል።

በዚህ የልማት እቅድ ላይ በከተማ ግብርናው ዘርፍ ትኩረት ተሠጥቶ ለመስራት የታሠበው በንብ ማነብ፣በዶሮ እርባታ፣ የጓሮ አትክልት ልማት እና ሌሎች ከግብርና ጋር ተያያዥነት ያላቸው ስራዎችን በስፋት ለመስራት የታሰበ ሲሆን የከተማ ግብርናን ማስፋት ከተቻለ የኑሮ ውድነትን ከማረጋጋት አንፃር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለውም ተጠቁሟል።

ይህን ውይይት የመሩት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ክብርት አዳነች አቤቤ በመድረኩ እንደተናገሩት ባለፈው ሦስት ወራት እቅድ አቅደን ወደ ተግባር በመግባት በርካታ ውጤቶች ማስመዝገብ ችለናል ያሉ ሲሆን ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የሌማት ትርፋትን በስፋት ለመስራትና ተግባራዊ ለማድረግ ምቹ ሁኔታ አለው መንግስት የጀመራቸውን ሰው ተኮር ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ከባለሀብቱ ጋር በቅንጅት መስራት ወሳኝ ነው ሲሉ በቀጣይ በክፍለ ከተማው የአገልግሎት አሠጣጥን ዲጂታላይዝድ ለማድረግና ያሉ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ ከክፍለ ከተማው ጋር በጋራ እንሠራለን ብለዋል።

Share this Post