20
Nov
2022
ዛሬ ከቀኑ 8:00 ጀምሮ አዲስ አበባ ከተማ በሁሉም ወረዳዎች በተጠና መንገድ በትምህርት ቤቶች ዙሪያ የመማር ማስተማሩን ሂደት እያወኩ ነው ባላቸው ድርጊት ፈፃሚ የንግድ ቤቶች ላይ የተለያዩ አስተዳደራዊ እርምጃዎች መወሰዱን የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮዎች ገለፀ ።
የቢሮው ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ አመሻሹ ላይ ዛሬ የተሰራውን የህግና የደንብ ማስከበር ሥራዎችን በማስመልከት ለሚዲያ አካላት በሰጡት መግለጫ ነው።
ኃላፊዋ አክለውም በ121 ወረዳዎች በ206 ትምህርት ቤቶች ዙሪያ የተለያዩ አዋኪ ድርጊቶችን የፈፀሙ 194 ጫት ቤቶች፣176 አረቄ ቤቶች፣21 ሕገወጥ ጋራዥ ቤቶች፣126 የላስቲክ ቤቶች ፣ 25 የሺሻ ቤቶች ፣እንዲሁም 244 ሌሎች የንግድ ቤቶችና የላስቲክ ቤቶች ላይ እርምጃ መወሰዱን ገልፀዋል።
ከእነዚህ ንግድ ቤቶች መካከል 99 ቤቶች እንዲታሸጉ መደረጉንም ኃላፊዋ ገልፀው እነዚህ ዛሬ እርምጃ የተወሰደባቸው የንግድ ቤቶች ተማሪዎች ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዳይከታተሉ የሚያደርጉ ከመሆናቸውም በላይ የሱስ ተገዢ የሚያደርጋቸው በመሆኑ እርምጃው ቀጣይነት ሁኔታ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።