ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ በበጎ ፍቃደኞች የሚገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታ መርሀ ግብር በይፋ አስጀምረዋል።

በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉና ድጋፍ የሚሹ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታ የመሠረተ ድንጋይ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ / አዳነች አቤቤ በዛሬው እለት በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የማስጀመሪያ መርሀ ግብር ተከናውኗል።

በዚህም መሠረት በክ/ከተማው አራት እያንዳንዳቸው ባለ አራት ወለል ህንፃዎችን በጠቅላላ 160ቤቶችን የሚይዝ የቤት ግንባታ የመሰረት ድንጋይ በከንቲባ አዳነች አቤቤ ተቀምጧል።

ሙሉ የቤቶቹ የግንባታ ወጪም የሚሸፈነው በበጎ ፍቃደኛ ኢትዮጵያውያን የጋራ ትብብር ሲሆን እነዚህም አያት ሪል ስቴት፤ ጊፍት ሪልስቴት ፤አልሳም ሪልስቴትና አምደሁን ጠቅላላ ንግድ MSW ሆራ ትሬዲንግ ይገኙበታል፡፡

መርሀ ግብሩን በይፋ ያስጀመሩት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ "ቤት ያረጃል ፤ይፈርሳል አስተሳሰቡ ግን ከትውልድ ትውልድ ይተላለፋል" ብለዋል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጨምረውም በዚህ የበጎ ፍቃድ ተግባር ላይ ተሳታፊ የሆኑ ባለሀብቶች መበልፀግ የምንችለው ህዝባችንን ይዘን ነው የሚል እሳቤን በመያዝ እያደረጉ ላለው የድጋፍ ተግባርም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ህዝቡም በዚህ አጋጣሚ አላግባብ ለመጠቀም በደላላ በተለያየ መንገድ የሚጥረውንም ሃይል ሃይ ሊል ይገባል በጋራ በማለት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

Share this Post