አዲስ አበባ መጋቢት 16 ቀን 2014 ዓ.ም
የመኖርያ ቤት ኪራይ ዋጋ ጭማሪንና ተከራዮችን ማስወጣትን ለመገደብ የወጣው ደንብ ለሚቀጥሉት ሶስት ወራት ተራዝሟል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የዜጎችን ጥያቄና አገራዊ ሁኔታን ከግምት ውስጥ በማስገባት ከዚህ በፊት የመኖርያ ቤት ተከራዮችን ለማስለቀቅና የመኖሪያ ቤት ኪራይ ጭማሪ ለመገደብ ደንብ ማውጣቱ ይታወቃል፡፡ ደንቡ ላለፉት ሶስት ወራትም እንዲራዘም ተደርጎ አንደነበርም አይዘነጋም፡፡
አሁንም ዜጎችን ከተለያዩ ጫናዎች ለመከላከል ሲባል ይህ ደንብ ለሚቀጥሉት ሶስት ወራት እንዲራዘም የከተማው አስተዳደር ወስኗል፡፡
በዚሁ መሰረት በሚቀጥሉት ሶስት ወራት ተከራዮችን ማስለቀቅና እና የቤት ኪራይ የዋጋ ጭማሪ ማድረግ የተከለከለ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ያስታውቃል፡፡በከተማችን ውስጥ የሚስተዋለውን የኑሮ ውድነት ችግር ለመቅረፍ ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ በዚሁ መሰረት ለሸማቾች የህብረት ስራ ማህበራት ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ በበድር መልክ ፋይናንስ ማቅረቡ፣ የገበያ ማዕከላትን የማበራከትና የእሁድ ገበያን በ16 ቦታዎች ተግባራዊ በማድረግ አምራቾችና ሸማቾች በቀጥታ ተገናኝተው እንዲገበያዩ በማድረግ እስካሁን ድረስ ለ19 ሳምንታት የእሁድ ገበያን በማካሔድ ከ120 ሚሊዮን ብር በላይ ግብይት መፈጸም ተችሏል፡፡
በትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም 2 ቢሊዮን ብር በመደጎም ከ628,000 በላይ ተማሪዎች የደምብ ልብስ እና ምገባ እየተደረገላቸው ይገናል፡፡ በዚሁ መሰረት ከ628,000 በላይ ተማሪዎችን በቀን ሁለት ጊዜ እየመገበ እገዛ እያደረገም ይገኛል፡፡
በስድስት የምገባ ማዕከላት አቅም የሌላቸው የከተማችን ነዋሪዎች በቀን አንድ ጊዜ እንዲመገቡ የሚያስችል አሰራር በመዘርጋት በቀን ከ12 ሺ በላይ የከተማችን ነዋሪዎች አንድ ጊዜ የሚመገቡበት ዕድል ተመቻችቷል፡፡
ለሸገር ዳቦ ከ818 ሚሊዮን ብር በላይ ድጎማ በማድረግ በቀን 1.5 ሚሊዮን ዳቦ ለከተማው ነዋሪ እንዲሰራጭ እየተደረገ ነው፡፡
ከ2013 እስከ 2014 ዓ.ም ድረስ በከተማችን 47.8 ሚሊዮን ሊትር ዘይት በድጎማ እንዲቀርብ የተደረገ መሆኑ እንዲሁም የትራንስፖርት አገልግሎቱን ለማሳለጥ ለአምበሳ፣ ለሸገር እና ድጋፍ ሰጪ አውቶቡሶች በአመት ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ ድጎማ እያደረገ መሆኑ፣ ወዘተ… ተግባራት የኑሮ ውድነቱን ለመቅረፍ የከተማ አስተዳደሩ ከሚያደርጋቸው ጥረቶች ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያዊ የመተሳሰብና የመተጋገዝ ባህላችንን በማሳደግ ፈታኝ ሁኔታዎች በጋራ ሆነን እንድንሻገር የከተማ አስተዳደሩ በዚህ አጋጣሚ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡