በአዲስ አበባ ከተማ በፅዳቱ ዘርፍ የተገኘውን ውጤትና ስኬት በዘላቂነት ለማስቀጠል ያለመ የሶስት ወራት የንቅናቄ ስራ በይፋ ማስጀመሪያ መርሐግብር በዛሬው እለት ተካሄደ።

በምክትል ከንቲባ ማእረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነ ' በፅዱ አካባቢ ለመኖር ሃላፊነቴን እወጣለሁ " በሚል በተዘጋጀ መድረክ ላይ የቀጣዩ ወራት የፅዳት ንቅናቄ አላማ በፅዳት ዘርፍ በአለምአቀፍ ደረጃ የተገኘውን ውጤት በተሟላ መልኩ ለማስቀጠል በተቀናጀ አሰራር ግንዛቤ በመፍጠር የነዋሪው ባህል ሆኖ እንዲዘልቅ ለማድረግ ነው ብለዋል።

አቶ ጥራቱ በየነ አክለውም የከተማውን ውበትና ፅዳት በማስጠበቅ የመጣውን አበረታች ለውጥ ህዝባዊ በማድረግ ከሚሰራው የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ ጎን ለጎን ከዚህ በኋላ ቆሻሻን ያለ አግባብ በሚጥሉ ግለሰቦችም ሆነ ድርጅቶች ላይ ተገቢው የህግ ተጠያቂነት እንዲሰፍን በተጠናከረ መልኩ እንሰራለን ሲሉም ተናግረዋል

አቶ ጥራቱ በየነ አዲስ አበባ የኢትዮጵያ መዲና፣ የአህጉሩና የአለምአቀፍ ተቋማት መቀመጫና የዲፕሎማቲክ ማእከል እንደመሆኗ ከተማዋን በሚመጥን ደረጃ ፅዳትና ውበቷን በተቀየረ አስተሳስብ በዘላቂነት አስጠብቆ ለመጪው ትውልድ በማስተላለፍ ታሪካዊ ሃላፊነታችንን በቅንጅት ልንወጣ ይገባል ሲሉም በአፅንኦት ገልፀዋል

በዚሁ የቀጣይ 3 ወራት የፅዳት ንቅናቄ በይፋ ማስጀመሪያ መድረክ ላይ ከአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን፣ ከደንብ ማስከበር ባለስልጣን፣ ከትራንስፖርት ቢሮ፣ ከምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባልስልጣንና ከሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተቋማት የተውጣጡ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተው በንቅናቄ መድረክ ላይ የወረዱ ተግባራት እንደየተቋማቸው ተጨባጭ ባህሪ በቅንጅት አስተሳስረው ለመፈፀም መግባባት ላይ ተደርሷል።

Share this Post