ህብረብሄራዊ አንድነታችን ለዘላቂ ሰላማችን!

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ዘንድሮ ለ17ኛ ጊዜ ህብረ ብሔራዊ አንድነታችን ለዘላቂ ሰላማችን በሚል መሪ ቃል የሚከበረውን የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀንን በማስመልከት በተማሪዎች መካከል ሲያካሂድ የቆየውን የጥያቄና መልስ ውድድር በዛሬው እለት አጠናቀቀ፡፡

የጥያቄና መልስ ውድድሩ ቀደም ብሎ ከትምህርት ቤት ጀምሮ ህገመንግስቱንና የፌደራል ስርአቱን መሰረት በማድረግ በቀረቡ ጥያቄዎች ተወዳድረው አሸናፊ ሆነው በቀረቡ 5 የአማርኛና 5 የአፋን ኦሮሞ ስርአተ ትምህርት 7 እና 8 ክፍል ተማሪዎች መካከል የተካሄደ ሲሆን በአሸናፊዎች አሸናፊ የማጠቃለያ ውድድሩ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ ወይዘሮ ቡዜና አልከድር፤ምክትል አፈጉባኤ ወይዘሪት ፋይዛ መሀመድ፤የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ፤በአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የሴቶችና ማህበራዊ ልማት ጉዳዮች ቃሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ዘይነባ ሽኩርን በየደረጃው የሚገኙ የትምህርት አመራሮችና ባለሙያዎች፤ወላጆች ፤መምህራን እና ተማሪዎችን ጨምሮ ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት ተካሂዱዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ ወይዘሮ ቡዜና አልከድር በጥያቄና መልስ ውድድሩ ማስጀመሪያ መርሀ ግብሩ ባስተላለፉት መልዕክት ዘንድሮ በሀገራችን 17 ጊዜ ህብረ ብሔራዊ አንድነታችን ለዘላቂ ሰላማችን በሚል መሪ ቃል የሚከበረውን የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀንን በማስመልከት በትምህርት ሴክተሩ በተለያዩ መርሀ ግብሮች ሲከበር ቆይቶ በዚህ መልኩ በተማሪዎች መካከል በሚካሄድ የጥያቄና መልስ ውድድር መጠናቀቁ የትምህርት ሴክተሩ የነገ ሀገር ተረካቢ ዜጎች የሚፈሩበት እንደመሆኑ ትውልዱ ህገመንግስቱንም ሆነ የፌደራል ስርአቱን በተመለከተ በቂ ግንዛቤ ኖሮት ጸረ ሰላም የሆኑና ለሀገር አንድነት እንቅፋት የሆኑ አስተሳሰቦችን መታገል እንዲችል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አስረድተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን መከበሩ በህገመንግስትና ህገመንግስታዊ ስርአቱ ዙሪያ ህብረተሰቡ የተሻለ ግንዛቤ እንዲያገኝ ከማስቻሉ በላይ በህዝቦች መካከል የእርስ በእርስ ግንኙነት በመፍጠር በጋራ የመኖር ኢትዮጵያዊ እሴቶችን ጠብቆ ለማስቀጠል የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ገልጸው የትምህርት ሴክተሩም ቀኑን በማስመልከት ከትምርት ቤት ጀምሮ በየደረጃው በተማሪዎች የጥያቄና መልስ ውድድር፤ በፓናል ውይይቶችና በተለያዩ ፌስቲቫሎች ሲያከበር መቆየቱን በመጥቀስ በአሉ ከትምህርት ቤት ጀምሮ በየደረጃው በድምቀት እንዲከበር ላስቻሉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በአሸናፊዎች አሸናፊ የማጠቃለያ ጥያቄና መልስ ውድድሩ በአማርኛው ስርዓተ ትምህርት 1 ተማሪ ነጂብ አማን ከአዲስ ከተማ 2 ተማሪ ፍቅር በሱፍቃድ ከአቃቂ ቃሊቲ ፤እንዲሁም 3 ተማሪ እያሱ በቀለ ከኮልፌ ቀራንዮ ክፍለከተማ አሸናፊ ሲሆኑ በአፋን ኦሮሞ ስርዓተ ትምህርት ደግሞ 1 ተማሪ ጨራ ሀብታሙ ከንፋስ ስልክ ላፍቶ 2 ተማሪ አጸደ ተካ ከቦሌ እንዲሁም ተማሪ ቤተሊሄም አዲሱ ከኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ 3 በመውጣት አሸናፊ ሆነው የተዘጋጀላቸውን ሽልማት ተቀብለዋል፡፡

Share this Post