የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በሶማሌ ክልል የሌማት ትሩፋት እንቅስቃሴን ማስጀመርያ ስነስርዓት ላይ ተገኝተዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩም ለክልሉ የሌማት ትሩፋት እንቅስቃሴ 110 የውሃ ፓምፖችን ድጋፍ አድርጓል፡፡

እንደ ሀገር የተጀመረውን የሌማት ትሩፋት እንቅስቃሴ በሶማሌ ክልል ለማስጀመር የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ / አዳነች አቤቤ ፤የክልሉ ፕሬዘዳንት አቶ ሙስጠፌ መሃመድ የመስኖና ቆላማ አካባዎች ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሃመድ ተገኝተዋል፡፡

በሰነስርዓቱ ላይ ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንደተናገሩት ክልሉ ያጋጠመውን ድርቅ ተቋቁሞ ዛሬ ለሌማት ትሩፋት በመድረሱ እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት እወዳለሁ ብለዋል፡፡

ሃገራችን እዚህ የደረሰችውና ለዛሬ የበቃችው የደም ዋጋ ተከፍሎላት ቢሆንም ነፃነቷ የፀና እንዲሆን ከድህነት በፍጥነት ሊያላቅቅ የሚችል ጠንካራ ኢኮኖሚ መገንባት ስንችል ነው ያሉት ከንቲባዋ በልመና ሃገራችን አትከብርም አትለወጥም ብለዋል፡፡

እንደ ከንቲባ / አዳነች አገላለፅ ክልሉ ያለውን የተፈጥሮ ፀጋና አቅም በትክክል መጠቀም ከተቻለ ክልሉ መላውን ኢትዮጵያ የመመገብ አቅም አለው ሲሉ ገልፀዋል፡፡ በተለይም በወተት ምርት መድሃኒትነት ያለውን የግመል ወተት ምርት በማምረት ለሌሎችም መትረፍ የሚችል ክልል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አዲስ አበባ የሁላችንም ከተማ እንደመሆኗ ለክልሉ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ምርቶች ገበያ እንድትሆን አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርጉም ገልፀዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የክልሉ የሌማት ትሩፋት ፕሮግራም እንዲጠናከር 110 ያህል የውሃ ፓምፖችን ድጋፍ በማድረግ ለክልሉ አስረክቧል፡፡

 

Share this Post