04
Nov
2022
አቶ ጥራቱ በየነ ዛሬ የከተማ አስተዳደሩ በወሳኝ ኩነት ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ ላይ እያካሄደ ያለው ሪፎርም እንዲሳካ ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን እንዲወጡ አቅጣጫ በተቀመጠበት መድረክ ላይ በመጪው ሳምንት ለሚጀመረው የመታወቂያ እድሳት በየደረጃው ያለው መዋቅር አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት እያጠናቀቀ መሆኑን ገልፀዋል።
በሁሉም ደረጃ የሚገኙ የአገልግሎት መስጫ ማእከላት ቀደም ተብሎ በተከናወነው የቅድመ ዝግጅት ተግባርና አሰራሩ መሰረት አገልግሎት ፈላጊውን ህብረተሰብ በቀናነትና በቅልጥፍና ማስተናገድ እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።
በዚሁ መድረክ ላይ የወሳኝ ኩነት ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ ሪፎርም ማካሄድ ያስፈለገው ተቋሙ ያጋጠመው ችግር የመልካም አስተዳደር ብቻ ሳይሆን የሃብትና የአገር ደህንነት ሰጋት ጭምር በመሆኑ ነው ያሉት አቶ ጥራቱ በየነ ችግሩን በውል ተረድቶ ለመፍትሔው በሚካሄደው ሪፎርም ሁሉም የበኩሉን አስተዋፅኦ መወጣት እንዳለበትም አስገንዝበዋል ።
የከተማ አስተዳደሩ የወሳኝ ኩነት ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ በአደረጃጀት፣ በሰው ሃይል፣ በቴክኖሎጅና በግብአት አሰራሩን በማዘመን ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት ለመስጠት እያካሄደ ላለው ወሳኝ ሪፎርም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ያላሰለሰ ድጋፍና ትብብር በማድረግ ሃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።