የአዲስ አበባ ከተማ የአደጋ ተጋላጭነትን ለመቀነስ በእሳት አደጋና ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በኩል እየተተገበረ ያለው ሪፎርም 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ወጭ እንደሚያስፈልገው ተገልጿል፡፡
ዶክተር ጀማሉ ጀምበሩ የአዲስ አበባ ከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ሃላፊ በተገኙበት በዛሬው እለት ኮሚሽኑ በአሰራር በአደረጃጀት በቴከኖሎጂ በግብአትና በሰው ሃይል እያካሄደ ያለውን ሪፎርም አስመልክቶ ለኢንሹራንስ ኩባንያዎች የስራ ሃላፊዎች ገለጻ ተደርጓል፡፡
በዚህ የውይይት መድረክ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ በየእለቱ ሰፊ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንሰቅስቃሴ የምታስተናግድ ከተማ እንደመሆኗ በየአመቱ 387 ሚሊዮን ብር ግምት ላለው ንብረትና ለሰው ህይወት ውድመት መንስኤ የሚሆን 535 ያህል የእሳት አደጋና ሌሎች ድንገተኛ አደጋዎች እንደሚከሰቱ የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ፍስሃ ጋርደው አስታውቀዋል፡፡
የከተማዋ ህዝብ ብዛት የደረሰችበትን የእድገት ደረጃ የሚመጥን የማሺነሪዎችና አደጋ መከላከል ሰራተኞች ጥምረት ከስታንደርዱ አንጻር አነስተኛ መሆኑን ተገልጿል፡፡
እንደ አብነትም በአዲስ አበባ በአሁኑ ወቅት የሚገኘው 9 የእሳት አደጋ መከላከል ጣቢያዎች ሲሆኑ በከተማዋ ስታንዳርድ መሰረት የሚያስፈልጋት 36 የእሳት አደጋ መከላከል ጣቢያ መሆኑም ተመላክቷል፡፡የእሳት አደጋ ማሺነሪዎችና አምቡላንሶች በተመሳሳይ ከሚጠበቀው ቁጥር ባነሰ ሁኔታ የሚገኝ በመሆኑ ስታንዳርዱ በሚጠይቀው መልኩ ይህንን ማሟላት እንደሚያስፈልግም አስረድተዋል።
የኢንሹራንሽ ኩባንያ ሃላፊዎች የእሳት አደጋና ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በየጊዜው እያደገችና እየዘመነች ላለችው አዲስ አበባ የሚመጥን የቅድመ አደጋ ስጋትና ተጋላጭነትን ለመከላከልና ለመቀነስ እያካሄደ ያለውን ሪፎርም አድንቀዋል።
ከተማ አስተዳደሩ የአደጋ ተጋላጭነትን ለመቀነስ እየተተገበረ ያለው ስር ስኬት አስፈላጊውን የፋይናንስ ፥የቴክኖሎጂና መሰል ድጋፎችን በተጠናከረ መልኩ ለመለገስ ቃል ገብተዋል።