የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአሜሪካ ኦሪገን በተካሄደ 18ኛው ዓለም ዐቀፍ የአትሌቲክስ ሻምፕዮና ላይ ሜዳሊያ ላመጡ አትሌቶች የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ እና የገንዘብ ሽልማት አበረከተ።

 

10 ሜዳሊያዎችን በማምጣት ከዓለም 2ኛ ከአፍሪካ 1ኛ በመሆን በድል ለተመለሰው ጀግናው የአትሌቲክስ ቡድናችን “አንድ ሆነን እንስራ፤ ኢትዮጵያ ታሸንፍ” በሚል መሪ ቃል የምስጋና እና የክብር መስጠት መርሃ-ግብር በማዘጋጃ ቤት የተለያዩ የፈደራልና የከተማ አስተዳደሩ የሥራ ሃላፊዎች በተገኙበት ተካሂዷል።የአ/አበባ ካቢኔ ሐምሌ 20/2014 ዓ/ም ባካሄደው አስቸኳይ ሰብሰባው በ18ኛው ዓለም ዐቀፍ የአትሌቲክስ ውድድር እንደየደረጃው ሜዳሊያ ላመጡ አትሌቶች በሽልማትነት እንዲሰጥ በወሰነው መሠረት በውድድሩ ላይ የወርቅ ሜዳሊያ ላመጡ ለእያንዳንዳቸው ስፋቱ 500ካ/ሜ፣ ለብር ሜዳሊያ 350 ካ/ሜ እንዲሁም የነሃስ ሜዳሊያ ላመጡ 250 ካ/ሜ የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ በምስጋናነት ተበረከቶላቸዋል።

ከተማ አስተዳደሩ ከዚህም በተጨማሪ በሻምፒዮናው ላይ ለተሳተፈው የልዑካን ቡድን በጥቅሉ የ10 ሚሊዮን ብር ሽልማት በጥሬ ገንዘብ አበርክቷል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በምስጋናና ክብር መስጠት መርሃ ግብር ባደረጉት ንግግር “ኢትዮጲያ የልጆቿ ገፅ ናት” ብለዋል። በድላችሁ ኢትዮጵያን ገፅታዋን ልታድሱ፥ ክብሯን በድል ልትገልጡ ፥ ሰንደቃችሁን አትማችሁ ኢትዮጵያን አስቀድማችሁ በ18 ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከፊት ስላቆማችሁን ደስ ብሎናል እንኳን ደስ አለን ብለዋል።

እኛ ኢትዮጵያውያን ፈተና የማይረታን፥ ይልቁንም የሚያፀናን ፥ መሰናከል የማያቆመን ይልቁንም አንድነታችንን የሚያጠናክሩን ህዝቦች መሆናችን ነጋሪ አያስፈልገንም ሲሉም ተናግርዋል ::

የሥነ ልቦና ስሪታችን ማሸነፍ ፥ በማሸነፍ ውስጥ አገርን ከፍ ማድረግ አንገታችን ቀና አድርገን በክብር አደባባይ መጓዝ ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች በ18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በድል የተመለሳችሁ እናንተ የሁለችንም የክብር ጌጥ ናችሁ ብለዋቸዋል።

በአሜሪካ አሪገን የተካሄው 18 ኛውን የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ውድድር በ 4 የወርቅ፣ 4 የብር፣ 2 የነሃስ፣ በድምሩ 10 ሜዳልያዎችን በመውሰድ ከአለም አዘጋጇን ሃገር አሜሪካንን በመከተል የ2ኛ ደረጃን በመሆን ማጠናቀቁ ይታወቃል።

Share this Post