የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ለ2015 በጀት ዓመት የ100.05 ቢሊዮን ብር የበጀት እቅዱ እንዲፀድቅ ለከተማው ምክር ቤት እንዲቀርብ ውሳኔ አሳልፏል::

 

ካቢኔው ዛሬ ማክሰኞ ሰኔ 21/2014 ዓ. ም ከአረንጓዴ አሻራ ማስጀመርያ መርሃ-ግብር መልስ ባካሄደው የ1ኛ ዓመት 11ኛ መደበኛ ስብሰበው በአጠቃላይ በከተማ አስተዳደሩ ከ2015 እስከ 2017 ዓመታትን ባካተተው የወጪ ማዕቀፍ ዕቅዱ ላይ የተወያየ ሲሆን ለ2015 በጀት ዓመት በከተማው ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ተዘጋጅቶ የቀረበውን የ100.05 ቢሊዮን ብር በጀትን ተቀብሎ በከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤት እንዲጸድቅ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

ከተያዘው በጀት ውስጥ 29.79 ቢሊዮን ብር ለክፍለ ከተሞች በድጎማ መልክ የሚሰጥ ሲሆን ቀሪው 70.26 ቢሊዮን ብር ደግሞ በከተማው በማዕከል ደረጃ ለአስፈጻሚ አካላት የተበጀተ ነው፡፡ከተያዘው በጀት ከፍተኛውን ድርሻ የያዘው ለፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያነት የሚውል የካፒታል በጀት ነው፡፡

ከተያዘው በጀት ዉስጥ 54.87 በመቶዉ የካፒታል በጀት ሲሆን 42.29 በመቶዉ ደግሞ ለመደበኛ ወጪዎች የሚውል ነው፡፡ ቀሪው 3.87 በመቶ በመጠባበቂያነት የተያዘ በጀት መሆኑ በእቅዱ ላይ ተመላክቷል፡፡

ረቂቅ በጀቱ ከ2014 በጀት ዓመት በ41.6 በመቶ አጠቃላይ እድገት ያሳየ ሲሆን በከተማ አስተዳደሩ የተቀመጡ ግቦችን ዉጤታማ ለማድረግ የመንግስት ሃብት ቅድሚያ ትኩረት ለተሰጣቸው ዘርፎች መሰረተ ልማት (Infrastructure); ለፈጠራ (Innovation) እና ለኢንዱስትሪ ዘርፍ ቅድሚያ በመስጠት

በመደልደል ሃብትን በቁጠባና ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመጠቀም ታስቦ የተዘጋጀ ነዉ፡፡

Share this Post