ም/ቤቱ በ3ኛ የአዲስ አበባ ም/ቤት 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 3ኛ እና የበጀት ዓመቱ ማጠቃላይ ላይ የቀረበለትን የ2015 በጀት ዓመት በጀት አፅድቋል።
የ2015 በጀት ዓመት እቅድ በለውጡ ሂደት የተቀመጡ የልማትና መልካም አሰተዳደር ሥራዎች ይበልጥ በማጠናከር ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ነው ተብሏል::ጥራት ያለው ኢኮኖሚ እንዲኖር ማረጋገጥ ፥ ምርትና ተወዳደሪነትን በማሳደግ ለዜጎች ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት በጥራት ማቅረብ ፣ ተቋማዊ ትራንስፎርሜሽን ማረጋገጥ ፥ የግሉ ዘርፍ ኢኮኖሚ መሪነት ማረጋገጥ ፥ የሴቶችና ወጣቶች ፍትሃዊ ተሳትፎ ማረጋገጥ ፥ የንፁህ መጠጥ ውሃ፣ መንገድ መሰረተ ልማት ፥ የዜጐች ሥራ እድል ፈጠራ ፥ የከተማ ውበት ማጠናከር ወዘተ በቀጣይ በጀት ዓመት ትኩረት የሚደረግባቸው መሆናቸውም ተገልጿል።
የታክስ ገቢ ማሳደግ ፥ከማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ ፥ ከመንገድ ፈንድ ወዘተ ገቢዎች እድገት ተይዟል።
ከተያዘው በጀት ከፍተኛውን ድርሻ የያዘው ለፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያነት የሚውል የካፒታል በጀት ነው፡፡
በጀቱ ከ2014 በጀት ዓመት በ41.6 በመቶ አጠቃላይ እድገት ያሳየ ሲሆን በከተማ አስተዳደሩ የተቀመጡ ግቦችን ዉጤታማ ለማድረግ የመንግስት ሃብት ቅድሚያ ትኩረት ለተሰጣቸው ዘርፎች መሰረተ ልማት (Infrastructure); ለውሃ ፥ መንገድ ፥ ለፈጠራ (Innovation) እና ለኢንዱስትሪ ዘርፍ ቅድሚያ በመስጠት በመደልደል ሃብትን በቁጠባና ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመጠቀም ታስቦ የተዘጋጀ ነዉ፡፡
በአጠቃላይ ከተማ አስተዳደሩ የተያዘውን በጀት ለልማትና መልካም አስተዳደር ሥራዎች ለማዋል ያቀደ ቢሆንም ሁሉንም የከተማውን ህዝብ የልማት ጥያቄና ፍላጎት በዚህ በጀት ብቻ መፍታት እንደማይቻል በመገንዘብ የከተማችን ነዋሪዎች ለአካባቢ ልማት ሥራዎችና ፀጥታ ትኩረት ሰጥቶ በመንቀሳቅስ የተቀመጡ ግቦች ለማሳካት ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ ተጠቁሟል ::
ም/ቤቱ ለ2015 በጀት ዓመት በከተማው ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ተዘጋጅቶ በመንግስት በበጀትና ወጪ አስተዳደር ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የቀረበውን የ100.05 ቢሊዮን ብር በጀትን ተቀብሎ አፅድቋል።