በ2013/2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና ወስደው በተለያዩ ኮሌጆች ስልጠና ያላገኙ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ዝግጅት ማድረጉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቴክኒክ ሙያ ስልጠና እና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ አስታውቋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቴክኒክ ሙያ ስልጠና እና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ እንደገለጹት የመማሪያ ክፍልችን እና ኮሌጆችን ለስልጠናው ምቹ ለማድረግ የህንጻ እድሳት እና የማሽነሪዎች ጥገና በማድረግ በ2015 በጀት ዓመት የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና ወስደው በተለያዩ ኮሌጆች ስልጠና ያላገኙ 33 ሺ 189 ተማሪዎችን ተቀብለው ለማስተማር ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
የቢሮው ኃላፊዋ ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ የ2013/2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና የወሰዱ ተማሪዎች በ2014 በነበረው የመቁረጫ ነጥብ መሰረት እንደሚስተናገዱም ነው የገለጹት፡፡
ሰልጣኝ ተማሪዎች ከደረጃ 1 አስከ ደረጃ 5 በተለያዩ 14 ኮሌጆች እድገት ተኮር በሆኑ 124 የሙያ ዘርፎች የሙያ ስልጠና ይሰጣልም ተብሏል፡፡
ስልጠና የሚሰጣቸው ተማሪዎች ከዚህ በፊት 12ኛ ክፍል አጠናቀው ቤታቸው የተቀመጡ ተማሪዎች ሲሆኑ ሴት ተማሪዎች በዚህ ስልጠና እንዲያልፉ በማድረግ ከስልጠና በኃላ የስራ እድል እንዲፈጠርላቸው እንደሚደረግም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቴክኒክ ሙያ ስልጠና እና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ ተናግረዋል፡፡
የቢሮው የስልጠና ልማት ዳይሮክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ታደለ አየነው በበኩላቸው በተፈጥሮ ሳይንስ እና በማህበራዊ ሳይንስ የ12ኛ ክፍል የመቁረጫ ነጥቡን የሚያሟሉ ተማሪዎች በቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኮሌጆች ስልጠና እንደሚሰጣቸው ገልጸዋል፡፡