በጠቅላላ ጉባኤው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አበቤና የተለያዩ የፌደራልና የክልል ምክር ቤት አፈጉባኤዎችና ም/ አፈ ጉባኤዎች ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የተገኙ ሲሆን ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት ‹‹መደራጀት ሃይል ነው፤ ግን መደራጀት በራሱ ግብ አይደለም ብለዋል፡፡ ስለሆነም ስንደራጅ በሚቀጠር በሚዳሰስ ስራዎች ማጀብ ይኖርብናል ሲሉ ገልፀዋል፡፡
በቀረን አራት አመት ለሚቀጥሉት የሴት ምክር ቤት አባላት የተሻለ ነገር ፈጥረን የምንሄድበት የተሻለ ስራ መስራት ይኖርብናል ያሉት ከንቲባ አዳነች ለዚህ ደግሞ ስንተባበርና ስንቻቻል፤ ከጥቃቅን አጀንዳዎች ይልቅ ዋና አላማችን ላይ ስናተኩር ነው በማለት አሳስበዋል፡፡
ሴቶች ጋር ያለምንም ማጋነን ፤የተለየ ርህራሄ፤ ችሎታ ፤ተሰጥኦ እናትነት አለ፤ይሄ ከትምህርት ጋር ሲዳብር ደግሞ ትልቅ ውጤት የሚያመጣ በመሆኑ በሚገባ በማስተባበር ለፍሬ ማድረስ የኮከሱ ትልቅ ተልእኮ መሆኑን አስምረውበታል፡፡
የአዲስ አበባ ምክር ቤት አፈጉባኤ ወ/ሮ ቡዜና አልቃድር፤ የሴቶችን ተሳትፎ ውስንነት ከፍ ለማድረግ ፤ለውጡ ለሴቶች የፈጠረውን መልካም እድል በላቀ ደረጃ በመጠቀም ከቃል ባለፈ ለከተማችን ብልፅግና ልንሰራ ይገባል ብለዋል፡፡
ኮከሱ የመሪነት ሚናውን እንዲወጣ ያሳሰቡት ወ/ሮ ቡዜና በምክር ቤቱ የተሻለ ልምድና አቅም ያላቸው ሴቶች በመኖራቸው የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ከቁጥር በዘለለ በተግባር ሊሰራ ይገባል ብለዋል፡፡