17
Nov
2023
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስራ ኢንተርፕራይዝና ኢንዲስትሪ ልማት ቢሮ ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር "ብቃት የወጣቶች የስራ ላይ ልምምድ መርሀ ግብር "ተሳታፊ 5193 ወጣቶችን በማስመረቅ የሁለተኛ ዙር ስልጠና አስጀምሯል::
በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት ምክትል ከንቲባና የስራ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ ከተማ አስተዳደሩ ለሰው ልጅ ሕይወት የመቀየር ፋይዳ ያላቸው ስራዎች አካል በሆነው የስራ ዕድል ፈጠራ ስራ በርካቶችን ከስራ በማገናኘት ራሳቸውን እንዲችሉና ሀብት እንዲፈጥሩ ማድረጉን ገልጸዋል::
የሰለጠነ የሰው ኃይል ዕጥረት እያለ ብዙዎች ስራ ፈላጊ የሆኑበት ሁኔታ ለማስተካከል ወጣቶችን ከኢንዱስትሪ ጋር በማገናኘት በአስተሳሰብ ተቀይረው በክህሎት በቅተው እጆቻቸውን ከስራ ማገናኘት ያስቻለው ይህ መርሀ ግብር በሁለተኛው ዙር መርሀ ግብር ከ15 ሺህ በላይ ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል::
አቶ ጃንጥራር መርሀ ግብሩ እንዲሳካ ሰልጣኞችን ተቀብለው በማሰልጠን ብቁ በማድረግና በመቅጠር አስተዋፅዖ ያበረከቱ ልበ-ቀና ተቋሞችን አመስግነው ወጣቶች ከተማ አስተዳደሩ በሚፈጥራቸው ዕድሎች በንቃት መሳተፍ እንዳለባቸው አሳስበዋል::