23
Nov
2022
የአብርሆት ቤተ መጻሕፍት ከነገ ህዳር 14 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ሌሊት 6 ሰዓት አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት ማጠናቀቁ ተገለጸ።
የአብርሆት ቤተ መጻሕፍት ዳይሬክተር ኢንጂነር ውባየሁ ማሞ እንዳሉት ቤተ መጻሕፍቱ ኢትዮጵያን የሚያኮራ ታሪክ ሰሪ ትውልድ በንባብ የሚገነባበት ማዕከል ነው።
በንግግርና ውይይት የሚያምን ትውልድ የሚገነባው አንባቢ ትውልድ ሲፈጠር መሆኑን ጠቅሰው፤ የአብርሆት ቤተ መጻሕፍት አንባቢ ትውልድን ለማፍራት ትልቅ ድርሻ አለው ብለዋል።
ቤተ መጻሕፍቱ ከዚህ ቀደም ከጧቱ 2 ሰዓት እስከ 12 ብቻ አገልግሎት ይሰጥ እንደነበር አውስተው ተጠቃሚዎች የአገልግሎት ሰዓት እንዲራዘም ሲጠይቁ እንደነበር አስታውሰዋል።
ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት አገልግሎት የሚሰጥበት ሰዓት ማሻሻያ መደረጉን ጠቅሰዋል።
በመሆኑም ከነገ ጀምሮ ከጧቱ 2 ሰዓት እስከ ሌሊቱ 6 ሰዓት ድረስ ቤተ መጻሕፍቱ ለህዝብ ክፍት እንደሚሆን ነው ያስታወቁት።