ከንቲባ አዳነች በዛሬው በሸገር ፓርክ መርቀው ለጎብኚዎች እይታ ክፍት ያደረጉት የሳይንስና ፈጠራ ኤግዚቢሽንና ዐውደ ርእይ ፤ የአዲስ አበባ ከአሥራ አንዱም ክፍለ ከተማ የተወጣጡ የተማሪዎችና መምህራን የፈጠራ ስራዎች ሉኡካን ያዘጋጇቸው ናቸው ።
በአውደ ርዕዩ መክፈቻ ላይ ላይ ንግግር ያደረጉት ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ እንደተናገሩት ተማሪዎችና መምህራን እየሰራችሁት ያለው ስራ ችግር ፈቺና ለሃገራችን ብልፅግና ጉዞ እውን መሆን ዋናውን መሰረት ለመጣል የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡
በከተማችን ለህዝብ ቃል የገባነው እንዲህ አይነት ቴክኖሎጂዎችን እውን በማድረግ ውስብስብ የአገልግሎት አሰጣጡንና በከተሞች በሌብነትና በዝርፊያ የሚባክነውን የህዝብ ሃብት ለልማት ማዋል እንችላለን በሚል ነው ያሉት ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች ዛሬ ያየነው የዚህ አላማ ውጤት ነው ፤የመማርን ችግር ፈቺነት በተግባር አሳይታችሁናል ብለዋል፡፡
እንደ ከንቲባዋ አገላፅ ተማሪዎች ባዶ የምሳ እቃ ይዘው የሚወድቁበት የነበረ ከተማ ዛሬ ቅድሚያ ለትምህርት ቅድሚያ ለትውልድ ብለን ጀመርነው ስራ ፍሬ እያፈራ ነው ሲሉ ገልፀዋል፡፡ተማሪዎች የእነርሱ ሃላፊነት ባልሆነ ፤የትምህርት ግብዓት ጎድሎባቸው አእምሯቸው ሲባክን ስናይ ነበረ ያሉት ከንቲባ አዳነች ዛሬ ግን በተሰራው ስራ በሃገር ደረጃ በከተማችን ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሚገቡ ተማሪዎች ብዛት አንደኛ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በሁሉም ረገድ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚመለከታችሁ አካላት በሙሉ የሳይንስና የፈጠራ ባለሙያዎችን ማበረታታት አለባችሁ ያሉት ከንቲባዋ፤ ባለሙያዎችም ከመቼውም ጊዜ በላይ የሚደረግላችሁን ድጋፍ በመጠቀም ችግር ፈች ምርምሮችን በርትታችሁ ልታደርጉ ይገባል ሲሉ ክብርት ከንቲባዋ ጥሪ አስተላልፈዋል።
የአዲስ አበባ ትምሕርት ቢሮ በዘላቂነት በሳይንስና ፈጠራ ስራዎች የዳበሩ ተማሪዎችን ለማብቃት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ለተማሪዎችና መምሕራን ሲያደርግ መቆየቱን የጠቀሱት የአዲስ አበባ ትምሕርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘላለም ሙላቱ በዘላቂነትም የፈጠራ ባለሙያዎችን ውጤታማ ለማድረግ ቢሮው እንደሚሰራ አስታወቀዋል።
የሳይንስና ፈጠራ ስራዎች ምርትና ምርታማነትን በከተማችንም ሆነ በአገራችን ለማሳደግ አስተዋጽኦቸው የጎላ ነው ያሉት የብሄራዊ ደሕንነት ዋና ዳይረክተር ዶክተር ሹመቴ ግዛው በዛሬው ዕለት የፈጠራ ስራቸውን ለእይታ ካቀረቡ ተማሪዎች መካከል ሦስት የተሻለ የፈጠራ ስራ ያቀረቡ ተማሪዎችን በተቋማቸው ተቀብለው ለመደገፍ ገብተዋል፡፡
የኢትዮጵያ የአርተፊሻል ኢንትለጀንስ ኃላፊ ኢንጅነር ወርቁ ጋቸና በበኩላቸው የሳይንስና ፈጠራ ባለሙያዎችን ለማበረታታት ከትምህርት ቢሮ ጋር ዘውትር በቅንጅት እንደሚሰሩ ጠቅሰው በተመሣሣይ የፈጠራ ሥራዎችን ካሳዩ ተማሪዎች መካከል አምስቱን ወስደው በተቋማቸው ለመደገፍ ቃል ገብተዋል
ዐውደ ርእዩ ከሰኔ ዘጠኝ እስከ 11 ቀን 2014 ድረስ እንደሚቆይ ተገልጿል፡፡