የሰባት (7) አዲስ የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከላት ግንባታ እየተጠናቀቀ ነው::

 

የከተማ አስተዳደሩ በቀን አንድ ጊዜ መመገብ የማይችሉ ዜጐችን መመገብ እንዲቻል 6 የተስፋ ብርሃን ምገባ ማዕከላትን አቋቁሞ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ውስጥ ያሉ የከተማዋ ነዋሪዎችን እየመገበ ይገኛል፡፡

አሁን ላይ በ6 ክፍለ ከተሞች (በአራዳ፣ ቦሌ፣ አዲስ ከተማ፣ ልደታ፣ ቂርቆስ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ) በየቀኑ ከ12 ሺህ በላይ ዜጎች እየተመገቡ ነው፡፡

በስድስቱ ማዕከላት የተጀመረው ዜጎችን የመመገብ ስራን ለማስፋት በአሁኑ ወቅት ተጨማሪ ሰባት (7) የምገባ ማዕከላት በጎፈቃደኞችን በማስተባበር በከተማ አስተዳደሩ እየተገነቡ ይገኛል፡፡ሰባቱ የምገባ ማዕከላት ሲጠናቀቁ በ13ቱ የምገባ ማዕከላት ከ30 ሺህ በላይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ዉስጥ ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሏል።የምገባ ማዕከላቱ በየቀኑ መመገብ ብቻም ሳይሆን የህይወት ክህሎት ስልጠና በመስጠት ዘላቂ የሆነ የተጠቃሚነት ስራዎችንም እያከናወነ ይገኛል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ዉስጥ የሚገኙትን የህብረተሰብ ክፍሎችን ከመመገብ በተጨማሪ ተማሪዎች ትምህርታቸው ላይ ብቻ ትኩረት እንዲያደርጉና የትምህርት ጥራትን ለመስጠበቅ ይረዳ ዘንድ በጀመረው የምገባ ፕሮግራም ከ628,000 በላይ ተማሪዎችን ቁርስና ምሳ እየመገበ ይገኛል፡፡ ተማሪዎችን ከመመገብ በተጨማሪ ለ799,930 ተማሪዎች የደንብ ልብስ ያቀርባል፡፡

በተስፋ ብርሃንና ትምህርት ቤቶች በሚሰራው የምገባ ፕሮግራም ለበርካታ እናቶች ሥራ ዕድል ለመፍጠር ችሏል፡፡ በዚህም በ777 ት/ቤቶች ላይ ብቻ ለ13,414 መጋቢ እናቶች የስራ እድል መፍጠር ተችሏል፡፡

Share this Post