“በሁከት እና ብጥብጥ የተሳተፉ 76 ግለሰቦችን በቁጥጥር ዋሉ”

 

 

በ1443ኛ የኢድ አልፈጥር በዓል ላይ በሁከትና ብጥብጥ በግንባር ቀደምትነት የተሳተፉ 76 ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታወቀ።

1443ኛ የኢድ አልፈጥር በዓል በአዲስ አበባ በሰፊ ፕሮግራም ታጅቦ በሰላማዊ ሁኔታ የተከናወነ ሲሆን ነገር ግን ጥቂት ከሀይማኖታዊ ሥርዓቱ ውጭ ሌላ የሁከትና ብጥብጥ ዓላማ ያላቸው ግለሰቦችና ቡድኖች ለብጥብጥ መነሻ በማይሆን ምክንያት ከስታዲዮም ውጭ በተለምዶ የቀይ ሽብር ሰማዕታት መታሰቢያ ሙዚየም አጠገብ ሆነው ባስነሱት ረብሻና ብጥብጥ በጸጥታ ኃይሎችና በንብረት ላይ ጉዳት የደረሰ ሲሆን 76 ግንባር ቀደም ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታውቋል።

የጋራ ግብረ ኃይሉ የኢድ አልፈጥርን በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ በቂ ዝግጅት አድርጎ ወደ ስምሪት መግባቱ ይታወቃል፡፡

በዓሉን ለማክበር ከወትሮው በተለየ መልኩ ህዝበ ሙስሊሙ በነቂስ ወደ በዓሉ ስፍራ በመሄድ የስግደት ስነ ስርዓቱ እንደ ተጀመረ ሁከትና ግርግር የተፈጠረ ሲሆን የፀጥታና ደህንነት ግብረ ሀይሉ መንስኤውን እየጣራ እንደሚገኝና ውጤቱንም ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግ ገልጿል፡፡

የጋራ ግብረ ኃይሉ ባደረገው ክትትልና ግምገማ አብዛኛው የበዓሉ ታዳሚ ስግደቱን ፈፅሞ የበዓሉን በረከት በመቋደስ ወደ ቤቱ ለመመለስ አስቦ የመጣ ቢሆንም አንዳንድ ግለሰቦችና ቡድኖች በቀልና ጥላቻን ቋጥረው እንዲሁም ከውስጥና ከውጭ ጠላቶቻችን ስውር ተልዕኮ ወስደው ሀገራችን የምትታወቅበትን የሀይማኖት መቻቻል በመናድ ህዝቡን በሀይማኖት በመከፋፈልና በመለያየት ሀገራችንን ለማፍረስ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች ግጭት በማባባስ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።

እነዚህ ፀረ-ሰላም ግለሰቦችና ቡድኖች ሀይማኖትን ሽፋን በማድረግ ተደራጅተው በአንዳንድ አካባቢዎች ስለታማ ነገሮችን፣ የውጭ ሀገር አክራሪዎችን አርማና የተለያዩ ግጭት ቀስቃሽ ጽሁፎችን በመያዝ ጥቃትና በቀል ለመፈፀም ወደ በዓሉ ስፍራ መምጣታቸውን ግብረ ኃይሉ በቁጥጥር ስር ካዋላቸው ፀረ-ሰላም ኃይሎች እጅ መያዙን ገልጿል። የፈጠሩትን ሁከትና ግርግር ተጠቅመው ከውስጥና ከውጭ ጠላቶቻችን የተቀበሉትን ስውር ተልዕኮ ለመፈፀም ጥረት አድርገዋልም ሲል ገልጿል፡፡

በዚህም የተነሳ የጸጥታ አካላት ላይ የአካል ጉዳት የደረሰ ሲሆን በህዝብና በመንግስት ተቋማት ላይም ጉዳት መድረሱ ታውቋል።

ይህንን እኩይ ተግባር ሲፈዕሙ የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይሉ ሁከቱን በትዕግስት በመከታተልና ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም በህዝበ ሙስሊሙ በተለይም በሴቶች፣ ህፃናትና በሰላማዊ የሀይማኖቱ ተከታዮች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ብርቱ ጥረትና ከፍተኛ ጥንቃቄ አድርጓል፡፡

ከዚህ ሁከትና ብጥብጥ ጋር በተያያዘ በግንባር ቀደምትነት የተሳተፉ 76 ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ያዋለ ሲሆን በቀጣይም ጉዳዩን በማጣራት ሌሎች የድርጊቱ ተሳታፊዎችን አድኖ በመያዝ ለህግ እንደሚያቀርብ ግብረ ኃይሉ አስታውቋል።

ግብረ ኃይሉ ክቡር የሰው ልጅ ህይወት እንዳይጠፋና የአካል ጉዳት እንዳይደርስ ከሰላም ወዳዱ የሙስሊም ህብረተሰብ ጋር በመሆን ከፍተኛ መስዋእትነት ከፍሎ መቆጣጠር የቻለ ሲሆን በበዓሉ ታዳሚዎች ላይ የሞትም ሆነ የአካል ጉዳት እንዳልደረሰ አረጋግጧል። ይህ ደግሞ የሀገራችን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይሉ ጥንካሬና ብቃት እንዲሁም ለህዝቡ ያለውን ወገንተኝነት ያረጋገጠ ነው ሲል ግብረ ኃይሉ ገልጿል፡፡

Share this Post