አዲስ አበባ ከተማ በትምህርት ቤት ምገባ ስራ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ማግኘቷን ተከትሎ የአፍሪካ ትምህርት ቤት ምገባ ቀንን እንድታስተናግድ ተመርጣለች፡፡ በዚህ መርሀ ግብር ለመሳተፍ የመጡ የዓለም ምግባ ፕሮግራም መሪዎች ፣ የአፍሪካ የትምህርት ሚኒስትሮች ፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች እና የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች የመቅደላ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን የምገባ ማዕከልን ጎብኝተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ በሁሉም የመንግስት ትምህርት ቤቶች ከሰባት መቶ ሺህ በላይ ተማሪዎች በቀን ሁለቴ በ14 የምገባ ማዕከላት ከ30 ሺህ በላይ አካል ጉዳተኞችና የሀገር ባለውለታ አረጋውያን በየቀኑ የምገባ አገልግሎት ያገኛሉ፡፡
ስራውን ስንጀምር በውስጥ ያለንን አቅም ተስፋ አድርገን ነበር ፤ በተግባር ያየነው ህዝቡ እርስ በራሱ ለመደጋገፍና መንግስት እየሰራቸው ያሉትን ስራዎች ለከተማችን ብልጽግና ያላቸውን ፋይዳ ተረድቶ ከጎናችን በመቆሙ ስራዎቻችን ፍሬ በማፍራት የከተማችንም ገጽታ መቀየር ጀምረዋል ያሉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ በትምህርት ቤት የምገባ ስራችን ዓለም የአፍሪካ ምርጥ መሆኑን አይቶ ተሞክሯችንን ለመቅሰም ማእከላቶቻችንን እያስጎበኘን ነው ብለዋል፡፡
ካርሜን በርባኖ በዓለም ምግብ ፕሮግራም የተማሪዎች ምገባ ዳይሬክተር በበኩላቸው ከተማ አስተዳደሩ በጀት መድቦ ተማሪዎች የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ በትምህርት ቤት የምገባ ማዕከል መክፈቱ የሚያስደነቅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በጉብኝቱ የተሳተፉት በዓለም ምግብ ፕሮግራም የአፍሪካ ዳይሬክተር ዶክተር ሀሚድ ኑሩ የመቅደላ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የተግባር ልምምድ የሚያደርጉበት የጓሮ አትክልት ልማት ለምገባ ማዕከሉ ግብዓት ማቅረብ ከማስቻሉም በላይ ተማሪዎች የተግባር ትምህርት እንዲያገኙየሚያስችል በመሆኑ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በምሳሌነት ሊጠቀስ የሚገባው ትልቅ ስራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የሌሴቶ ትምህርትና ስልጠና ሚኒስትር ፕሮፌሰር ንቶኢ ራፓፓ በበኩላቸው ተማሪዎች በየቀኑ የመመገብ ስራ መስራቱ መንግስት ለትውልድ ግንባታ የሰጠቀውን ትኩረት የሚያሳይ በመሆኑ ከዚህ ትልቅ ስራ ትምህርት ቀስመናል ብለዋል፡፡